Mols.gov.et

በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሥራ የሚያቆሙ ኢንተርፕራይዞችን …

March 19, 2026
በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ሥራ የሚያቆሙ ኢንተርፕራይዞችን ዳግም ወደ ሥራ ለመመለስ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በመተባበር፣ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ሥራ የሚያቆሙ ወጣትና ሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል። ፕሮጀክቱ ኢንተርፕራይዞቹ የገጠሟቸውን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ዳግም ወደ ምርትና አገልግሎት እንዲገቡ በማድረግ፣ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻልና የአካባቢዎችን የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እንደሚያስችል ተመላክቷል። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ዕድል ፈጠራ ማስፋፊያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘሪሁን ዓለማየሁ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ በቅርቡ የጸደቀውን የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ በኢኮኖሚ ቀውስና በአደጋ ወቅት የኢንተርፕራይዞችን ተጎጂነት ለመቀነስ ፖሊሲው ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ ወጣቶችንና ሴቶችን መልሶ ለማቋቋም እንደሚረዳ ገልጸዋል። ይህም ሚኒስቴሩ የፖሊሲ ማዕቀፎችን ወደ ተጨባጭ የሥራ ዕድልና የኢኮኖሚ ድጋፍ ለመቀየር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል። በአፍሪካ ልማት ባንክ የሀገር ውስጥ ፕሮግራም ኦፊሰር ፓዋልም ኢልቡዶ በበኩላቸው፤ ባንኩ የአፍሪካን ወጣቶች የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ወደ ኢኮኖሚያዊ ኃይል ለመለወጥ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ይህ ፕሮጀክት ዘላቂ የሥራ ዕድልና ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል። የፕሮጀክቱን ዝርዝር አፈጻጸም በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አሺቅ በድሩ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ ለአራት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን በአጠቃላይ 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በጀት ተመድቦለታል። ከዚህም ውስጥ 10 በመቶው በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ይሆናል። ፕሮጀክቱ በዋናነት በአማራ፣ በአፋር፣ በትግራይ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በሶማሌ ክልሎች የሚገኙ ከ3,000 በላይ ኢንተርፕራይዞችን በፋይናንስ አቅርቦት፣ በክህሎት ማሳደጊያ ሥልጠናን ጨምሮ በተለያዩ ድጋፎች ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top