ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ እምቅ አቅም ያለው የቱሪዝም ዘርፍ
March 26, 2026
ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ እምቅ አቅም ያለው የቱሪዝም ዘርፍ
የቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ እምቅ አቅም መነሻ በማድረግ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስልጠናዎችን በተቀናጀ መልኩ እየሠጠ እንደሚገኝ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ የሥራ አጥነትን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍና የኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስልታዊ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
የኢንስቲትዩቱ የምርምርና ማማከር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይታሰብ ስዩም እንደገለጹት፤ የቱሪዝም ዘርፍ በባህሪው ሰፊ የሰው ኃይል የሚፈልግ በመሆኑ፣ ኢንስቲትዩቱ የሚሰጣቸው ስልጠናዎች ከገበያው ተጨባጭ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣሙ እየተደረገ ነው።
በተለይም ወጣቶች በዘርፉ ሰልጥነው ሲወጡ የራሳቸውን ቢዝነስ እንዲጀምሩ የሚያስችል የክህሎትና የሥራ ፈጠራ ስልጠናዎችን በማቀናጀት፣ ዜጎች መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ከመሸፈን ባለፈ ለሌሎችም የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበት ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ይታሰብ አክለውም፣ አሁን ላይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ የቱሪዝም ቴክኖሎጂዎችን በስልጠና ክፍሎቹ በማስተዋወቅ ሰልጣኞች በዘመናዊ መንገድ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን ብቃት እንዲላበሱ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

