ሪፎርምን ወደ ዘላቂ ተቋማዊ ለውጥ ማሸጋገር
August 19, 2026
ሪፎርምን ወደ ዘላቂ ተቋማዊ ለውጥ ማሸጋገር የቀጣዩ የሪፎርም ምዕራፍ ዋና ትኩረት ነው
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና በተቋሙ በተካሄደው የሥራ ባህል ጥናት (Ecosystem Survey) ውጤት ላይ የሚኒስቴሩ አመራርና ሠራተኞች ውይይት አካሂደዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሚፈሪሃት ካሚል በውይይቱ ላይ እንደገለፁት፣ ሚኒስቴሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ባካሄደው ሰፊ ሪፎርም ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ተጨባጭና ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ ይህም ሪፎርሙ በተግባር ምላሽ መስጠት መጀመሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
የተመዘገበው ውጤት የመጨረሻ መዳረሻ ሳይሆን ለቀጣይ የላቀ አፈፃፀም መነሻ መሆኑን ጠቁመው፣ “ያስመዘገብነውን ውጤት ወደ ዘላቂ ተቋማዊ ለውጥ እንዴት እንቀይራለን?” የሚለው ጥያቄ የቀጣዩ የሪፎርም ምዕራፍ ዋና ትኩረት መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዚህም ተቋሙ ለዜጎች እርካታን፣ ለሠራተኞች የሙያዊ ኩራትን እና ለሀገር የላቀ አፈፃፀምን የሚያመነጭ ተቋም መሆን እንዳለበት ገልፀው ይህንን ለማሳካት በየደረጃው ያሉ የአሠራር፣ የመዋቅርና የተቋማዊ ባህል ክፍተቶችን በመለየት ማረም፣ ማሻሻልና በተከታታይ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሪፎርሙ የመጨረሻ መለኪያም በዜጎች ሕይወት ላይ የሚፈጥረው የሚታይ፣ የሚለካና ዘላቂ ጠቀሜታ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም የቀጣዩ የሪፎርም ትኩረት የተመዘገበውን ውጤት የሚያስቀጥል ተቋማዊ ባህል፣ ውጤታማነትን የሚያረጋግጥ ሥርዓት፣ የሚያስተሳስር አሠራር እና ዘላቂ ተቋማዊ አቅም መገንባት መሆኑን ገልፀዋል።
ለዚህም የሚኒስቴሩአመራርና ባለሙያዎች በጋራ ርብርብ ማድረግ እና በተጠያቂነት መንፈስ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።












