Mols.gov.et

“ሥራ ፈጣሪዎች እንጂ ሥራ ፈላጊዎች እንደማትሆኑ ሙሉ እምነት አለኝ” ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

August 12, 2026
“ሥራ ፈጣሪዎች እንጂ ሥራ ፈላጊዎች እንደማትሆኑ ሙሉ እምነት አለኝ” ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በደረጃ 6 እና 7 በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1,875 ስልጠና አጠናቃቂዎች በደማቅ ሥነ-ሥርዓት አስመርቋል። የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል፣ ትምህርትና ስልጠና የሰውን አቅም ለማዳበርና ለተሻለ የወደፊት ሕይወት ለመዘጋጀት የሚያግዙ መሠረቶች መሆናቸውን ገልጸዋል። “ትምህርትና ስልጠና በየደረስንበት ምዕራፍ ሙሉ ሰው እንድንሆን፣ መጪው ጊዜያችን ብሩህ እንዲሆን የሚያዘጋጁን የስንቅ ማዕዶቻችን ናቸው” ብለዋል። ክብርት ሚኒስትር ተመራቂዎቹ ዛሬ ለዚህ ደረጃ የደረሱት በቀላሉ እንዳልሆነ ጠቁመው፣ ብዙ ሌሊቶችን በማጥናት፣ ብዙ ሰዓታትን በመሥራት፣ በጽናትና በትዕግስት እንዲሁም ከቤተሰብና ከልጆች ናፍቆት ጋር በመታገል ያለፉት ሂደቶች የጽናት፣ የብርታትና የዲሲፕሊን ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል። “ዛሬ ነጋችሁን ምን ያህል ብሩህ እንደሆነ አጉልቶ የሚያሳይ ዕለት ነው” ሲሉም ተመራቂዎቹን አበረታተዋል። ስልጠናም ሆነ ትምህርት የሀገርን እምቅ አቅም ለማውጣት፣ የሀገርን ችግር ለመፍታት እንዲውሉ ማድረግ ከተቻለ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ ጉዞ ውስጥ ዘርፉ የማይተካ ሚናውን መወጣት xንደሚችልም አብራርተዋል፡፡ በዚህ የለውጥ ጉዞ የቴክኒክና ሙያ ዘርፉ ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ከማፍራት ባሻገር፣ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በመፍጠር የሀገር ልማትን እንዲያግዝ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። የዘርፉን አቅም ለማሳደግም እንደ ክህሎት ፓርክ (Skill Park) ያሉ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ እነዚህ ልማቶች ዘርፉን ወደ ላቀ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግሩም ገልጸዋል። “ሥራ ፈጣሪዎች እንጂ ሥራ ፈላጊዎች እንደማትሆኑም ሙሉ እምነት አለኝ” ሲሉም ለተመራቂዎቹ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ክብርት ሚኒስትር ለተመራቂዎች ስኬት የወላጆች፣ የቤተሰብ፣ የመምህራንና የኢንስቲትዩቱ አመራሮች አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ጠቁመው ምስጋና አቅርበዋል። በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የሰላም ቴክኒክና ሙያ መሥራች ወ/ሮ ፀሐይ ሮሺሊ ልዩ የእውቅና ሽልማት ተበርክቷል።
en_USEN
Scroll to Top