Mols.gov.et

መሶብ፡ የእፎይታ ማዕከል

November 5, 2025
መሶብ፡ የእፎይታ ማዕከል አቶ ብሩክ በሚሠራበት ተቋም ውስጥ ተቀጥረው ለሚያገለግሉ የውጭ ሀገር ዜጎች የሥራ ፈቃድ ለማውጣት፣ ለማሳደስና ለማሰረዝ በየጊዜው አገልግሎቱን ይሰጡ ወደነበሩ ተቋማት ይመላለስ እንደነበረ ይናገራል፡፡ ወ/ሮ ትብለፅም በተመሳሳይ በምትሠራበት ካምፓኒ ከ 200 በላይ ቻይናውያን መኖራቸውን ትናገራለች፡፡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በሌለበት ሁኔታ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የውጭ ሀገር ዜጎች ጉዳይ ማስፈፅም እጅግ ፈታኝ መሆኑን ትገልፃለች፡፡ አቶ አብዲማ ደግሞ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ግንኙነት ቡድን መሪ ናቸው ፡፡ እሳቸውም በዩኒቨርሲቲያቸው ውስጥ እያገለገሉ የሚገኙ ህንዳውያንን የሥራ ፈቃድ ጉዳይ ለማስፈፀም ለበርካታ ዓመታት ወደ አዲስ አበባ ይመላለሱ እንደነበረ በማስታወስ የሚወስድባቸው የተራዘመ ጊዜ ለብዙ ችግርና እንግልት ይዳርጋቸው እንደነበረም ይናገራሉ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት አገልግሎቱ የሚሰጠው ማኑዋል በሆነ መልኩ ስለነበር ፋይል መፈለግ፣ ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል በነበረው ምልልስ ሳቢያ አንድን ጉዳይ ለማስፈፀም ከሁለት ሳምንት በላይ ይፈጅባቸው እንደነበር ሦስቱም ተገልጋዮች ያስታውሳሉ፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተቋቋመ በኋላ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (E-LMIS) አማካኝነት የሚሰጥ መሆኑ በተወሰነም ደረጃ ሥራውን አቀላጥፎት እንደነበር የሚገልፁት ተገልጋዮች ነገር ግን የተወሰኑ አገልግሎቶች በተለያየ ቦታ የሚሰጡ መሆናቸውበአሠራር ፍጥነት ላይ የራሱ የሆነ ተፅ ዕኖ እንደነበረው ይናገራሉ፡፡ ዛሬ ሦስቱም ባለጉዳዮች ቅልጥፍናን ከፍጥነት ጋር አጣምሮ በያዘው የ‹‹መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት›› ተገኝተዋል፡፡ ከጋምቤላ ከአንድ ቀን በፊት መምጣታቸውን የሚናገሩት አቶ አብዲማ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ዲጂታል በሆነ መልኩ በመጫናቸው ከግማሽ ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ጉዳያቸውን ማጠናቀቃቸውን ይገልፃሉ፡፡ ‹‹ከዓመታት በፊት የነበረውን ውጣውረድ ለሚያውቅ ሰው ይህ በእጅጉ ህልም ነው›› የሚሉት አቶ አብዲማ አሠራሩ ወደ ዲጂታል ከማደጉ በላይ የማዕከሉ ባለሙያዎች ብቃትና ሥነ ምግባርም አገልግሎቱን የበለጠ ምቹ እንዳደረገው ይናገራሉ፡፡ ‹‹እንደ እኔ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የውጭ ሀገር ዜጎች ጉዳይ ለሚያስፈፅም ሰው ፍጥነትና ቅልጥፍና በእጅጉ ወሳኝ ነው›› የምትለው ትብለፅ በመሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በተገኘች በውሱን ደቂቃዎች ውስጥ ጉዳዩዋን ማጠናቀቅ መቻሏ ህይወቷን በእጅጉ እንዳቀለለውም ትናገራለች፡፡ ‹‹ላለፉት ስምንት ዓመታት አንድን ጉዳይ ለማስፈፀም ለሳምንታትና ለወራት እመላለስ ነበር›› የሚለው አቶ ብሩክም በበኩሉ በመሶብ አንድ ማዕከል ያገኘው አገልግሎት ጉልበቱንና ጊዜውን በእጅጉ እንደቆጠበለት በፈገግታ ታጅቦ ይናገራል፡፡ በ‹‹መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት›› የተጀመረው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ክትትልና ትኩረት እንደሚፈልግ የሚናገሩት ሦስቱም ባለጉዳዮች በቀጣይ ሁሉም መንግስታዊ ተቋማት የአገልግሎት ደረጃቸውን ለማሻሻል ‹‹መሶብ መልካም አርዓያ የሆነ ተቋም ነው ›› በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top