Mols.gov.et

ስምምነቱ ኢትዮጵያ በጋራ መልማትን …

January 2, 2024
” ስምምነቱ ኢትዮጵያ በጋራ መልማትን ያስቀደመች ሀገር መሆኗን ያረጋገጠ ነው” ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ምክንያት በማድረግ ደስታቸውን የገለጹበት መድረክ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት የህዝብ ቁጥራችን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ኢኮኖሚያችንም ግዙፍ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ወደ መሆን እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡ ይህ በመሆኑም የቀይ ባህርንና የወደብ አስፈላጊነት አጀንዳ የህልውና ጉዳይ ሆኗል፡፡ መንግስት ለጉዳዩ ሌሎች እንደሚሉት በሀይል ሳይሆን ጥበብ በተሞላበት ዲፕሎማሲ እልባት ለመስጠት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል ብለዋል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ያደረጉት ስምምነት ለዘመናት ወደብ አልባ ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ እና ለቀጣዩ ትውልድ ትርጉም ያለው የታሪክ እጥፋቶች መካከል አንዱ እንደሆነም ነው የጠቆሙት፡፡ በተገኘው ፍጹም ሰላማዊ እና የዲፕሎማሲያዊ ስኬት እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት ክብርት ሚኒስትር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰጡት ጥበብ የተሞላበትና ቁርጠኛ አመራር ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አሁን ላይ በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ቢሆንም መነሻው ድህነት እንሆነ የጠቆሙት ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከድህነት ጋር ያለንን ዝምድና ለማቆም ከመቼው ጊዜ በላይ መትጋት፣ መደማመጥ እና መከባበር የሚጠበቅብን ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡ ለዚህም ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top