Mols.gov.et

ፕሮግራሙ ለበርካታ ማህበራዊና…

December 31, 2023
“ፕሮግራሙ ለበርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶችን ህይወት ከመታደግ አንፃር ጉልህ አስተዋፅኦ አለው።” ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ወጣቶች በተመረጡ ተቋማት የሥራ ላይ ልምምድ አድርገው ወደ ቅጥር ሥራ እንዲሰማሩ ለማስቻል በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እየተተገበረ የሚገኘው ‹‹ብቃት የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም›› የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አፈፃፀም ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ የሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ‹‹ብቃት የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም›› ለበርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶችን ህይወት ከመታደግ አንፃር ጉልህ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡ ሴቶች ለድህነት ያላቸውን ተጋላጭነት ከግምት በማስገባት 60 በመቶ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ልጅ ያላቸው 27 በመቶ እናቶችም ተገቢውን ትኩረት አግኝተውና ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል የፕሮግራሙ ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአገራችን በሚገኙና ለሥራ አጥነት ተጋላጭ በሆኑ አስራ አንድ ከተሞች ላይ በዓለም ባንክ ትብብር እየተተገበረ የሚገኘው ይህ ፕሮግራም እድሜያቸው ከ18 እስከ 25 የሚሆን ወጣቶች ስለ ሥራ ያላቸውን አመለካከት ለማነፅ የሚያስችል ሥልጠና ሰጥቶ ለቅጥር ሥራ ከማዘጋጀት፣ በመንግሥትና በግል ድርጅቶች መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ከማሳደግ እና ሥራ ላይ ልምምድ ስረርዓት በኢትዮጵያ ባህል እንዲሆን ከማስቻል አንፃር ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ክቡር አቶ ንጉሡ አብራርተዋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር የፕሮግራሙ አፈፃፀም ለተጠቃሚነት ተመዝግበውና ሥልጠና ወስደው በሥራ ላይ ልምምድ ከቆዩ ወጣቶች መካከል 82 በመቶ የሚሆኑት ቋሚ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው በመድረኩ ተገጿል፡፡ በሁለተኛው ዙር የፕሮግራሙ ትግበራ ለሥልጠና ጥራት ትኩረት መስጠት፣ ፕሮግራሙ በተቀመጠለት ስታንዳርድ መሰረት መተግበሩን እና የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው መከታተል ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ ኃላፈነት መሆኑን ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በአፅንኦት አንስተዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top