ፕሮጀክቱ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ አካል ሂደት ነው፡፡ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
October 30, 2025
ፕሮጀክቱ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ አካል ሂደት ነው፡፡
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የተመረቱ ተኪ ምርት ቴክኖሎጂዎች ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ሙሉ ለሙሉ የተመረተ ኢንዳክሽን ሞተር፣ ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጀር እና ስማርት ፖልን ጨምሮ የተለያዩ ዲጂታል መተግበሪያዎች ለእይታ ቀርበዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በምንሰራቸው ሥራዎች ውስጥ ሁሉ በርካታ ማነቆዎች አሉ፡፡
እነዚህ ችግሮችን ስናውቃቸው፣ ስንተባበርና ስንተጋገዝ ወደ ዕድል ይቀየራሉ፡፡ የዚህ አይነት ፕሮጀክቶች የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ አካል ሂደት ነው ብለዋል።
ያለንበት የዲጂታል ዘመን እንደመሆኑ ይንን ተገንዝቦ እዚህ ላይ የሚሰራ ተቋም ረዥም ርቀት መሄድና የሀገር የጀርባ አጥንት ሆኖ ማገልገል እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ትልቅ ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም እንደሆነ ያመላከቱት ክብርት ሚኒስትር ይህን ተልዕኮውን በመደመር እሳቤ እውን እንዳደረጉትም ጠቁመዋል፡፡
ተኪ ምርቶቹ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ቴክኖሎጂዎቻቸውን እንዲያጎለብቱና ለገበያ እንዲያቀርቡ ለማስቻል የተቀረፀው የ‹‹ክህሎት ኢትዮጵያ›› መርሃ ግብር ውጤት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
‹‹ክህሎት ኢትዮጵያ›› ላለፉት ሁለት አመታት በጣም ትልልቅ ሥራዎች የተሠሩበት፤ በርካታ ቴክኖሎጂዎች የመነጩበትና ለሀገር የጀርባ አጥንት የሆኑ ለኢኮኖሚያዊ አስተዋጾ ያላቸው ሥራዎች የተሠሩበት መሆኑንም ክብርት ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡
መሰል ቴክኖሎጂዎች ለበርካታ ዜጎች ሥራ ዕድል መፍጠሪያ አማራጭ ሆነው የሚያገለግሉ ከመሆኑ በላይ የተለያዩ አምራች ኢንተርፕራይዞችም ሥራቸውን በቀላሉ በቴክኖሎጂ ታግዘው ማከናወን እንዲችሉ ከማድረግ አንፃር ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳላቸውም ተገልጿል፡፡
ቴክኖሎጂዎቹ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን በማሳደግ የሀገርን ኢኮኖሚ የመገንባት አቅም ያላቸው በመሆኑ ለሚፈጥሩ አእምሮዎችና ለሚሠሩ እጆች ዕድል መስጠት እንደሚያስፈልግም ክብርት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል አሳስበዋል፡፡ ለዚህ ውጤት መገኘት እንደ ዘርፋቸው እንደ ሙያቸው አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል፡፡









