Mols.gov.et

ፈጠራንና ፍጥነትን ያማከለው የሸገር የሥራ ዕድል ፈጠራ ተሞክሮ …

November 25, 2024
ፈጠራንና ፍጥነትን ያማከለው የሸገር የሥራ ዕድል ፈጠራ ተሞክሮ … በዘርፉ የተደረገውን ሪፎርም ተከትሎ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎቻችን የዜጎችን እለታዊ ችግሮች ከመቅረፍ ባሻገር ጥሪት ማፍራት እና ሀብት መፍጠር ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል፡፡ የሚፈጠረው የሥራ ዕድልም እሴት ሰንሰለትን፣ ፈጠራ እና ፍጥነትን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን አቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የኦሮሚያ ሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮም ይህን አቅጣጫ ተግባረዊ በማድረግ በዘርፉ ተጨባጭ ሥራዎችን መሬት ላይ ማውረድ ችሏል፡፡ ለበርካታ ወጣቶችም የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡ በክልሉ የሸገር ከተማ አስተዳደር ለከተማው ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የመንግስትን በጀት ሳይጠብቅ እየሄደበት ያለው ርቀት በዘርፉ ለሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጭምር ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ሥራ መሆኑን ሰሞኑን በከተማው የተገኘው የፌዴራል የድጋፍና ክትትል ቡድን ተመልክቷል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን በዘርፉ ትልቅ ፈተና ሆኖ የሚገኘውን የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ችግር ለመቅረፍም የመስሪያና የመሸጫ የሼዶች ግንባታ እያከናወነ ይገኛል፡፡ በ21 ሄክታር ላይ ያረፈው የመጀመሪያው የግብርና ክላስተር ሼዶች ግንባታ በያዝነው በጀት ዓመት መስከረም መር የተጀመረ ነው፡፡ አሁን ላይ የማጠናቀቂያ ምዕራፉ ላይ ይገኛል፡፡ 300 የሚሆኑ ሼዶችን ያቀፈው ይህ ክላስተር እሴት ሰንሰለትን መሰረት ያደረገ የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲያስችል ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚህም ሼዱ ከመኖ ማቀነባበሪያና የእንስሳት ጤና ኬላ ጀምሮ እሴት የሚያክሉና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን በሙሉ እንዲያቀፍ ተደርጎ የተገነባ ነው፡፡ በመልካ ናኖ ክፍለ ከተማ እየተሰራ ያለው ይህ ግንባታ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የሀገር በቀል ሙያዎች ክላስተር ሼዶችን ጨምሮ የትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋማት ግንባታ እና የኮሊደር ልማትን ጨምሮ አጠቃላይ ወጪው 2.5 ቢሊየን እንደሚጠጋ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህን ፕሮጀክት ከሌሎች ተመሳሳይ ሥራዎች ልዩ የሚያደርገው ምንም አይነት የመንግስት በጀትን ያልጠየቀና ሙሉ ለሙሉ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚሰራ እንዲሁም በፍጥነትና በጥራት የተገነባ መሆኑ እንደሆነም የከተማው አመራሮች ለድጋፍና ክትትል ቡደኑ ገልፀዋል፡፡ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፉ የሚስተዋለውን የግብዓትና ግብይት ችግርን ለመቅረፍም ክላስተሩ የመኖ ማቀነባበሪያ እና የመሸጫ ቦታዎችም እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡ ከክላስተሩ ባለፈ በከተማው 181 በላይ ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበትና የሚሸጡበት G + 6 የገበያ ማዕከል በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ቀን ተሌት ርብርብ እያደጉ ይገኛል፡፡ ይህ ፕሮጀክት የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር የሥራ ባህላችንንም ጭምር እንድንቀይር እድል ፈጥሮልናል የሚሉት የከተማው አመራሮች ሥራው በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወን ሁሉም የከተማ አስተዳድሩ አመራሮች ርብርብ እያደረጉ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ የተመራው የድጋፍና ክትትል ቡድንም ከሼዱንና ከገበያ ማዕከሉን በተጨማሪ የቡራዩ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅን፣ የፋም ውሃ ፋብሪካን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከልን እና ለውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ሥልጠና እየሰጠ የሚገኝውን ሀባቦ የቤት አያያዝ ማሰልጠኛ ተቋምን ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ነቢሃ መሃመድ ከጉብኝቱ በኳላ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋት አኳያ ሚናቸው የላቀ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥልና ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሊሰፋ ይገባል ብለዋል፡፡ ለክልሉ እና ለከተማ አስተዳደሩ አመራሮችም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰጡ ላለው ቁርጠኛ አመራርም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top