ጉባኤው በድጅታል ኢኮኖሚው ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም የሚያስችል ልምድና ተሞክሮ የተገኘበትና የታሰበውን ግብ ያሳካ መሆኑ ተገለፀ
October 13, 2023
ጉባኤው በድጅታል ኢኮኖሚው ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም የሚያስችል ልምድና ተሞክሮ የተገኘበትና የታሰበውን ግብ ያሳካ መሆኑ ተገለፀ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሎራንዶና አሶሼትስ እና ከፍሎውለስ ኢቨንትና ጋር በመተባበር ያተዘጋጀው እንቆጳ ጉባኤ ተጠናቋል፡፡
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር በለጠ ሞላ እንደገለጹት፤ በሀገራችን ያለው የስታርት አፕ ስነ-ምህዳር በተለያዩ ተግዳሮቶች የታጠረ ነው፡፡
እነኚህን ተግዳሮቶች ለመሻገር የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላቱ ጋር በመሆን በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ስታርት አፖች ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱበት ስነ -ምህዳር ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
ለተግባራዊነቱም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ሌሎች አስፈፃሚና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ ይገኛል፡፡
ለሁለት ተከታታይ ቀናት የተካሄደው የእንቆጳ ጉባኤም ትስስር መፍጠር የሚያስችል እና በዘርፉ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን በጋራ መሻገር የሚያስችል ነው፡፡
ስለሆነም ሀገራችንን ወደፊት የሚያራምድ ለቴክኖሎጂ፣ ለኢኖቬሽንና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ምቹ የሆነ ስነ-ምህዳር በጋራ መገንባት እንደምንችል ያመላክታል ብለዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው መንግስት ለሥራ ፈጣሪዎች እና ሀሳብ ላላቸው ጀማሪ ቢዝነሶች እንዲሁም ለግሉ ዘርፍ ተዋንያን ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና ማነቆዎችን የመፍታት ሚናውን ለመወጣት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው፡፡
ከእነዚህ ሥራዎች መካከልም ከህዳር እስከ ህዳር በሚል መሪ ሀሳብ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ያስጀመረው የኢንተርፕሪነርሺፕ ስነ-ምህዳር ግንባታ አንዱና ዋነኛው ሲሆን የእንቆጳ ጉባኤም የዚሁ ሥራ አንዱ አካል ነው፡፡
ጉባኤው በድጅታል ኢኮኖሚ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም የሚያስችል ልምድና ተሞክሮ የተገኘበትና የታሰበውን ግብ ያሳካ ነው ብለዋል፡፡
በጉባኤው የነበሩ ውይይቶችም በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና ሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ለዘርፉ ልማት በጋራ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ልምድ የተወሰደበት እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና ሥራ ዕድል ፈጠራ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥን የሚጠይቁ በመሆናቸው የብዙሃን መገናኛ ድርጅቶች በዘርፉ አነቃቂና አስተማሪ የሆኑ ፕሮግራሞችን መስራት እንደሚገባቸው የጠቆሙት ክቡር አቶ ንጉሡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በዚህ ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡
መንግስት ስነ-ምህዳሩን ምቹ ለማድረግና በግሉ ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ምቹ ሁነታዎችን ከመፍጠር፣ ማነቆዎችን ከመፍታት ባለፈ በጋራ እንደሚሰራም ነው ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ጨምረው የገለፁት፡፡
በጉባኤ የተለያዩ ሥራ ፈጣሪዎች፣ ቴክኖሎጂ አልሚዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ጀማሪ የንግድ ሥራ ባለሙያዎች፣ ኢንቨስተሮች እንዲሁም የትምህርትና የፋይናንስ ተቋማት የተወጣጡ 100 ተወያዮች የተሳተፉበት የፓናል ውይይትና ትስስር የሚፈጥሩበት ኤግዚቢሽን ተካሂዷል፡፡