የፈንላንድ የልማት ትብብርና የውጭ ንግድ ሚንስትር …
June 11, 2024
የፈንላንድ የልማት ትብብርና የውጭ ንግድ ሚንስትር ክቡር ቪሌ ታቪዮ የኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩትን ጎበኙ፡፡
በፊንላንድ የልማት ትብብርና የውጭ ንግድ ሚንስትር ክቡር ቪሌ ታቪዮ የተመራ የልዑካን ቡድን በኢፌዲሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አካሂዷል፡፡ ልዑኩ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ፣ በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር፣ እና ሌሎች አባላትን አካትቷል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ከድር ሚንስትሩን ተቀብለው የፊንላንድ መንግስትና ህዝብ ለኢንስቲትዩቱ እያደረጉ ያለውን ድጋፍ እና የወደ ፊት የትብብር ዕቅዳቸውን አቅርበዋል፡፡
ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ1960ዎቹ ጀምሮ በትምህርት፣ በግብርና፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በሌሎችም ዘርፈ ብዙ የልማት ትብብር ጉዳዮች አብረው ሲሰሩ መቆታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ሥርዓተ ስልጠናን ዘመናዊ ለማድረግ የአሰልጣኞች የአቅም ግንባታ ስራ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው (MOPEDE) ፕሮጀክት ባለፉት አራት ዓመታት ለኢንስቲትዩቱ የአይሲቲ መሰረተ-ልማት እያሟላ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ፕሮጀክቱ የአሰልጣኞች አቅም ግንባታ ላይ ሰፊ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ በተጨማሪም ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዘመናዊ ዲጂታል ስቱዲዮ ገንብቶ ማስረከቡን ገልጸዋል፡፡
ሚንስትሩ ቪሌ ታቪዮ በበኩለቸው በአገራቸው ድጋፍ የተሰሩ ዲጂታል ስቱዲዮዎችን፣ ስልጠና ያገኙ እና በዚህም ዲጂታል ኮንተንት እያዘጋጁ ያሉ አሰልጣኞችን ካዩ በኋላ አብረው መስራት በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በትምርትና ስልጠና ዲጂታይዜሽን አገራቸው የዳበረ ልምድ ያላት መሆኑት የጠቀሱት ሚንስትሩ የኢንስቲትዩቱ አሰልጣኞች አቅማቸውን በመገንባት ለኢንዱስትሪ አቅም የሚሆኑ ብቁ ሙያተኞችን ማፍራት እንዲችሉ አገራቸው አጠንክራ ትሰራለች ብለዋል፡፡