Mols.gov.et

የጎዳና ላይ የዶሮ ጥብስ ቢዝነስ ሥራ …

April 13, 2024
“ዛሬ ያስጀመርነው የጎዳና ላይ የዶሮ ጥብስ ቢዝነስ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ባለፈ ከሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩ ጋር በቀጥታ የሚተሳሰርና ሁሉም ዜጋ የዶሮ ሥጋን በቀላሉ ማግኘት የሚችልበትን ዕድል የሚፈጥር ነው።” ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሀዋሳ ከተማ ሁለተኛውን የጎዳና ላይ የዶሮ ጥብስ ቢዝነስን በይፋ አስጀምሯል፡፡ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ መንግስት ለሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለዜጎች ምቹ፣ አስተማማኝና ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሰፊ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ በሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከዚህ በፊት ከዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በአዳማ ከተማ የመጀመሪያውን የጎዳና ላይ የዶሮ ጥብስ ቢዝነስ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ይህም ከሥራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር መንግስት በሥራ ባህል እና በስነ ምግብ የበለጸገ ትውልድ ለመገንባት በሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ከግምት ውስጥ በማስገባት ሥራውን ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋት ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ዛሬ ያስጀመርነው የጎዳና ላይ የዶሮ ጥብስ ቢዝነስ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ባለፈ ከሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩ ጋር በቀጥታ የሚተሳሰርና ሁሉም ዜጋ የዶሮ ሥጋን በቀላሉ ማግኘት የሚችልበትን ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡ እሴት ሰንሰለትን መሰረት ባደረገው የሥራ ዕድል ፈጠራ አቅጣጫችን መሰረት ሥራው በዶሮ እርባታ፣ በዶሮ መኖና ሥጋ አቅርቦት እንዲሁም በዶሮ ጤና አጠባበቅ ጋር ተያይዞ ሊፈጥር የሚችለው የሥራ ዕድል በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ነው ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የጠቆሙት፡፡ ስለሆነም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች የጎዳና ላይ የዶሮ ጥብስ ቢዝነሱን ፍላጎቱ ወዳለበት አካባቢ ለማስፋት፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና በዘርፉ በርካታ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፤ በሂደቱም የዜጎቸን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡ በእለቱ የጎዳና ላይ የዶሮ ጥብስ ቢዝነስ ከማስጀመር ባለፈ በሀዋሳ ከተማ በመናኸሪያ ክፍለ-ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ እድሳት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት የተደረገ ሲሆን በከተማው ውጤታማ የሆኑ ኢንተርፕራይዞች ተጎብኝተዋል፡፡
Scroll to Top