የዲጅታልና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አርበኛ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ ነው። ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
October 25, 2025
የዲጅታልና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አርበኛ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ ነው።
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ፣ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት በተሰጠው ትኩረት የዲጂታልና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አርበኛ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በ4ኛው ዙር ሰመር ካምፕ በሳይበር ደህንነትና ተያያዥ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶችን አስመርቋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በዲጂታል ዘመን ወቅቱን የዋጀ በክህሎት መር እውቀት የሠለጠነ ዜጋን ማፍራት ለሀገር ዕድገት ወሳኝ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶታል።
የተሟላ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሳይበር ደህንነትና ዘመኑ የሚፈልገውን የቴክኖሎጂ እውቀት የታጠቁ ወጣቶችን በተከታታይ የማሰልጠንና የማሰማራት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ስራ ለመስራት በሰው ኃብት ልማት በተለይ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ወጣቶች አቅም ለማጎልበት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
የሳይበር ጥቃትን በብቃት የሚከላከልና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ህልምን የሚያሳካ የዲጂታል አርበኛ የሆነ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ በዲጂታል ዘርፉ ላይ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል እያደረገች ላለው ሽግግር በሳይበር ደህንነት ዘርፍ የበቃ የሰው ኃይል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ፕሮግራም ዋና ዓላማ በዘርፉ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ታዳጊዎችና ወጣቶች ክህሎት በማሳደግና በዘርፉ ለሀገር የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራዊ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ አስተዳደሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፥ ወቅቱን የሚመጥን ብቁ፤ ዕውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የሳይበር ታለንት ስልጠና አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪ ትስስር በመፍጠርና በተቋሙ የሚሰሩ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች እውቅና እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የፈጠራ ስራዎችን የበለጠ ለማጠናከር የሚያግዝ የሥራ ፈጣሪዎች አቅም ማጎልበቻ ማዕከል ከፍቶ ወደ ስራ ማስገባቱን ገልጸዋል።
በዚህ በሰመር ካምፕ የፈጠራ ስራ ያላቸው ታዳጊዎች በማዕከሉ ውስጥ የፈጠራ ስራቸውን ማስፋትና ወደ ገበያ የሚያቀርቡበትን ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በሰመር ካምፑ ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች በበኩላቸው በቆይታቸው የተለያዩ ክህሎቶች ማግኘታቸውን ገልጸው በቀጣይ ሀገራቸውን በዲጂታል ዘርፎች ለማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
ወጣት አሌክሳንደር ሳሙኤል እንደተናገረው የኢ-ለርኒንግ ስርዓት ማበልጸጉን በማንሳት፥ የጀመረው ሥራ የትምህርት ስርዓቱን በዲጂታል ለማሳለጥ ዓላማ ያለው ነው ብሏል።
ሌላው ወጣት ኬና ቶልቻ በቆይታው በኤሮስፔስ ዘርፍ ስልጠና መውሰዱን በመግለፅ፥ በድሮን ኦፕሬሽን ላይ እውቀት መቅሰሙን ጠቁሟል።
ወጣት ባስሌል መስፍን በበኩሉ በሶፍትዌር ማበልፀግ ስልጠና እንድወሰደ ጠቅሶ፥ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የተጓዦችን ህዝብ ትራንስፖርት አጠቃቀም የሚያሳልጥ መተግበሪያ መስራታቸውን ገልጸዋል። ዘገባው የኢዜአ ነው።








