የዓለም ባንክ ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
April 30, 2024
የዓለም ባንክ ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ከዓአለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካ የማህበራዊ ጥበቃና ሥራ አተገባበር ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሮበርት ቼዝ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ እንደገለጹት፤ መንግስት ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማላቅ ስርዓቱን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በዓለም ባንክ ድጋፍ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም በመጀመሪያ ዙር የሥራ ላይ ልምምድ ካደረጉ ወጣቶች መካከል 93 በመቶ ከሥራ ጋር ማስተሳሰር መቻሉንም አመላክተዋል፡፡
18 የሚሆኑ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን በረጃ የማሻሻል እና በከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ውጤታማ ሥራዎች እንደተከናወኑ ያመላከቱት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ባንኩ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠየቀዋል፡፡
የዓአለም ባንክ የምስራቅ አፍሪካ የማህበራዊ ጥበቃና ሥራ አተገባበር ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሮበርት ቼዝ በበኩላቸው፤ በመጀመሪያው ዙር በወጣች የሥራ ላይ ልምምድ የተገኘው ውጤት የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታሳቢ በማድረግ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው የከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ የሚሆን እንደሆነም አመላክተዋል፡፡
በጨረታ ሂደት የሚስተዋሉ መዘግየቶችን በመቅረፍ ባንኩ ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ የሚያደርገውን ድጋፍም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
ከውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አኳያ የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማሰማራት የተጀመሩ ሥራዎችን ያደነቁት ዶ/ር ሮበርት ቼዝ ለዓለም የሥራ ገበያ የሚቀርበው የሰው ሃይል የመዳረሻ ሀገራትን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ስልጠና እንዲሰጥና እንደ ጀርመን ያሉ ሀገራትን ታሳቢ አድርጎ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡