የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም ሁለተኛ ዙር ትግበራ ተጀመረ
January 16, 2024
የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም ሁለተኛ ዙር ትግበራ ተጀመረ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርና ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በአሥር ከተሞች ላይ የሚተገብረው ‹‹ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም›› ሁለተኛ ዙር ትግበራ በይፋ ተጀምሯል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የሥራ ፣ የሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በሁለተኛው ዙር ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ትምህርታቸውን በተለያየ ምክንያት ያቋረጡ ወጣቶች በሥራ ገበያው ላይ ተወዳዳሪ ከመሆን አንፃር የለባቸውን ክፍተት የሚሞላ የሥራ ላይ ልምምድ አድርገው የቅጥር ሥራ እንዲያገኙ ለማስቻል ተግባራዊ የተደረገ ፕሮግራም ነው›› ብለዋል፡፡
ወጣቶችን በአመለካከትና በክህሎት በመቅረፅ በቅጥር ሥራ ላይ እንዲሠማሩ ከማስቻል አንፃር በአንደኛው ዙር የፕሮግራሙ አፈፃፀም በርካታ ተሞክሮዎች መገኘታቸውን የጠቆሙት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ከዚህ አንፃር በሁለተኛው ዙር የፕሮግራሙ ትግበራ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡፡
የፕሮግራሙን ተጠቃሚዎችን በአግባቡ ከመመዝገብ፣ ሥልጠናውና የሥራ ላይ ልምምዱ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት ተግባራዊ መደረጉን በንቃት ከመከታተልና የሥራ ላይ ልምምድ ያደረጉ ወጣቶች በቅጥር ሥራ ላይ እንዲሠማሩ ተገቢውን ርብርብ ከማድረግ አንፃር ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ክቡር አቶ ንጉሡ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡
በአንደኛው ዙር የፕሮግራሙ ትግበራ የሥራ ላይ ልምምድ ላደረጉ 12, 452 ወጣቶች የቅጥር ሥራ በማመቻቸት የዕቅዱን 93 በመቶ ማሳካት የተቻለ መሆኑ በመድረኩ የተገለፀ ሲሆን በሁለተኛው ዙር የፕሮግራሙ ትግበራ 23, 773 ወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ አድርገው በቅጥር ሥራ ላይ እንዲሠማሩ የሚያስችል ዕቅድ መያዙም ተገልጿል፡፡