Mols.gov.et

የኢንተርፕሪነርሺፕ ሳምንት የ2023 ኢትዮ ስፐርስ ውድድር…

December 8, 2023
የኢንተርፕሪነርሺፕ ሳምንት የ2023 ኢትዮ ስፐርስ ውድድር አሸናፊዎችን በመሸለም ተጠናቀቀ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችና ስታርትአፖች ምቹ ስነ ምህዳር ለመፍጠር ከህዳር እስከ ህዳር በሚል ከሚያካሂደው የንቅናቄ ስራዎች አንዱ በሆነው የዓለም የኢንተርፕሪነርሺፕ ሳምንት ከህዳር 24 2016 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲካሄዱ ቆይቷል፡፡ ‹‹ለኢንተርፕሪነሮች ፤ ክፍት ይሁኑ በሮች ›› በሚል መሪ ሃሳብ ሲካሄድ የነበረው ይህ መድረክ ኢትዮ ስፐርስ 2023 የንግድ ማስፋፊያ የቢዝነስ ዕቅድ ውድድር አሸናፊዎችን በመሸለም ተጠናቋል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም በሆነው የኢትዮጵያ ኢንተርፕሪነርሽፕ ኢኒስቲቲውት ሲካሄድ በቆየው የኢትዮ ስፐርስ 2023 ውድድር አንድ ሺ የሚሆኑ የአነስተኛና የመካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ተሳትፈውበታል፡፡ የውድድሩ አምስት አሸናፊዎች ከአምስት መቶ እስከ አንድ መቶ ሺ ብር የተሸለሙ ሲሆን የተሻለ ተወዳዳሪ የነበሩ አስር ሴት ተወዳዳሪዎች ደግሞ እያንዳንዳቸው የዋንጫና የአንድ መቶ ሺ ብር ማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በማጠቃለያ ስነ-ስርዓቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ፣ የሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ባስተላለፉት መልዕክት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተከበረው የኢንተርፕሪነርሺፕ ሳምንት የተሳካና በርካታ ትምህርት የተወሰደበት ነው ብለዋል፡፡ ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የዘርፉ ተዋንያን አገራችን የኢንተርፕራይዞች መፈልፈያና የኢንተርፕሪነሮች መፍለቂያ እንደትሆን በራቸውን እንዲከፈቱና የየበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
Scroll to Top