Mols.gov.et

የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፉ ለሀገራዊ የልማት ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥና ዘመኑን የዋጀ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

December 18, 2024
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፉ ለሀገራዊ የልማት ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥና ዘመኑን የዋጀ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ አመራርና ሠራተኞች ከተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን በአዲስ መልክ እየተከለሱ በሚገኙት የቴክኒክና ሙያ አዋጅና ስትራቴጂ ረቂቅ ሰነዶች ላይ ውይይት አካሄዱ፡፡ ውይይቱን የመሩት የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) ከዓመታት በፊት ሥራ ላይ የዋሉት የቴክኒክና ሙያ ስልጠና አዋጅና ስትራቴጂዎች ለዘርፉ መሰረት መጣል ያስቻሉ መሆኑን ገልፀው ነገር ግን ወቅታዊ ከሆነው ሀገራዊ ፍላጎትና የአሠራር ስርዓት አንፃር መሻሻል ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች ተለይተው እየተሠራባቸው ቆይቷል። ይህም የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፉ ለሀገራዊ የልማት ፍላጎት ምላሽ የሚሰጥና ዘመኑን የዋጀ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል። የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አስተዳደርን ማብቃት፣ ሥልጠና ጥራትንና ተገቢነትን ማረጋገጥ፣ ተፈላጊነትን ማሳደግና ፈጠራን ማዕከል ያደረገ ስነ -ምህዳር መገንባት የአዲሱ ስትራቴጂ ዋንኛ ምሰሶዎች መሆናቸው በመድረኩ በቀረበው ገለፃ ላይ ተብራርቷል፡፡ በቀረበው ገለፃ በእያንዳንዱ ምሰሶ ውስጥ የተካተቱ ቁልፍ ጉዳዮች በዝርዝር የቀረቡ ሲሆን ከፖሊሲና የህግ ማዕቀፎች፣ ከተቋማት አደረጃጀት፣ ከባለድርሻ አካላት ቅንጅት፣ ከፋይናንስ ስርዓት፣ ከስልጠና ጥራት ፣ከተደራሽነትና ተያያዥ ጉዳዮች አንፃር ሊታዩ የሚገቡ ሃሳቦች በተሳታፊዎች አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ተሻለ በሬቻ(ዶ/ር) የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂው ከአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲና ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ራዕይና ተልዕኮ ጋር መተሳሰር እንደሚኖርበት በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top