‹‹የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ችግር ፈቺ እና መፍትሄ አመንጪ በመሆኑ ለሀገር ዕድገት ትልቅ ፋይዳ ያለው ዘርፍ ነው››
July 6, 2024
‹‹የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ችግር ፈቺ እና መፍትሄ አመንጪ በመሆኑ ለሀገር ዕድገት ትልቅ ፋይዳ ያለው ዘርፍ ነው››
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ከ2100 ሰልጣኞችን በመጀመሪያ(ደረጃ 6) እና በሁለተኛ (ደረጃ 7) ዲግሪ ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስክ ችግር ፈቺ እና መፍትሄ አመንጪ በመሆኑ ለሀገር ዕድገት ትልቅ ፋይዳ ያለው ዘርፍ ነው፡፡
ዘርፉ እንደ ሀገር ያለምናቸውን ግቦች ከማሳካት አንፃር የሚያበረክተውን ጉልህ አስተዋፅኦ ከግምት በማስገባትም የፖሊሲ ማዕቀፍ በመቅረፅ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ሥርዓትን ችግር ፈቺና መፍትሔ አመንጪ እንዲሆን ለማስቻል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አዳዲስ የለውጥ እሳቤዎችን ቀርፆ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡
ይህም የሥልጠና ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ቁልፍ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑንም አንስተዋል።
በዘርፉ የሚሰጠውን ስልጠና ዘመኑ በደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ በማሳደግ መላው ዜጎች በተመሳሳይ የክህሎት ልማት ራሳቸውን እንዲያበቁ በሚያስችል መልኩ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
ሥልጠና ለቀጣዩ የህይወት ምዕራፍ ጉልበትን፣ ዕውቀትን እና ጥበብን የሚያጎናፅፍ ትልቅ ዕድል መሆኑን ያመላከቱት ክብርት ሚኒስትር ተመራቂዎች በደረሱበት ደረጃ ብቻ ረክተውና ተወስነው ሳይቀሩ ለራሳቸውና ለሀገራቸው ትርጉም ያለው ሥራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።