የተገልጋዮችን እርካታ 95 ከመቶ በላይ ማድረስ ያስቻለው ማዕከል
October 26, 2025
የተገልጋዮችን እርካታ 95 ከመቶ በላይ ማድረስ ያስቻለው ማዕከል
ቴክኖሎጂ የሥራ ቅልጥፍናን፣ ምርታማነትንና ውጤታማነት ያሳድጋል፡፡ ፈጠራና ፍጥነትን ማዕከል ባደረገው አቅጣጫ መንግስት ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለዜጎች ለማቅረብ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ፣ ምቹ እና ቀልጣፋ ለማድረግ አገልግሎቶቹን በቴክኖሎጂ አስተሳስሮ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡
በፌዴራል ደረጃ ባለው ማዕክል 23 ተቋማት አገልግሎታቸውን በማዕከሉ አስገብተዋል፡፡ ከእነዚ ተቋማት መካከል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚገኝ ሲሆን የውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሥራ ፈቃድ እና የዲጂታል ኢንተርፕራይዝ ምስረታ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች በማዕከሉ እየተሰጡ ይገኛል፡፡
የ100 ቀናት የሥራ አፈፃፀም ላይ እንደተመላከተው በማዕከሉ 180 አገልግሎቶች ባሳለፍነው መቶ ቀናቶች ብቻ ተሰጥተዋል፡፡ ከ79 ሺህ በላይ ተገልጋዮችም በማዕከሉ አገልግሎት እንዳገኙና በማዕከሉ አገልግሎት ካገኙ ዜጎች በተወሰደ መረጃም የእርካታ ደረጃቸው 95 በመቶ በላይ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
በብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ የተሰጡ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ክቡር አቶ አደም ፋራህ በሰጡት ማብራሪያ የመንግስት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት በቴክኖሎጂ አግዞ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግና ብልሹ አሰራርን ለመቀነስ መንግስት በልዩ ትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
በፌዴራል ደረጃ ወደ ሥራ ከገባው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በተጨማሪ ወደ ክልሎች እንዲሰፋ አቅጣጫ ተቀምጦ በዚህም በተለያዩ የክልል ከተሞች ማዕከሉን ወደ ሥራ ማስገባት እንደተቻለም አብራርተዋል፡፡
መሶብ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን በዘላቂነት ከመፍታት፣ ብልሹ አሰራርን ከማስቀረት እና የተገልጋይ እርካታን ከማሳደግ አኳያ ፋይዳው ትልቅ መሆኑን ያብራሩት ክቡር አቶ አደም ፋራህ እስከ ሰኔ 2018 ድረስ ማዕከላቱን 100 ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡
ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም ፤
