Mols.gov.et

የተናበበ ትብብር- የተጠናከረ አጋርነት

October 17, 2024
የተናበበ ትብብር- የተጠናከረ አጋርነት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የሥራ ኃላፊዎችና የፕሮግራም አስተባባሪዎች ጋር በሥራ ፈጠራና ክህሎት ልማት ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል፡፡ በመድረኩ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከናወኑ አበይት ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን እንዲሁም የዘርፉ አዳዲስ እሳቤዎችን የሚያመላክት ሰነድ በክብርት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ቀርጓል፡፡ በዚህም በሦስት ዓመታት ውስጥ በሀገር ውስጥ ከ9 ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የገለፁት ክብርት ሚኒስትር በውስጥ አቅም ለምቶ ወደ ሥራ በገባው የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት አማካኝነት ከ517 ሺ በላይ ለሆኑ ዜጎች በውጭ ሀገራት የሥራ ዕድል መፈጠሩ ጠቁመዋል፡፡ ዜጎች ከሀገራቸው ሳይወጡ በውጭ ሀገር በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ላይ ተሳታፊ የሚሆኑበት የርቀት የሥራ ዕድል 83ሺ ለሚሆኑ ዜጎች መፈጠሩንና 26ሺ ያህሉ በተጨባጭ ወደ ሥራ መግባታቸውን አንስተዋል፡፡ አምራች ኢንተርፕራይዞች ምርታቸውን የዲጂታል አማራጮችን ጭምር በመጠቀም የሚያስተዋውቁበትና የሚሸጡበት ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ኢምፖሪየም ግንባታ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡ የኢንተርፕረነርሺፕ ልማትን በማጠናከር የኢትዮጵያን ችግር የሚፈቱ ሚሊዮን ኢንተርፕሪነሮችን ለማፍራት የሚያስችል ሥርዓት በሚኒስቴር መ/ቤቱ እየተዘረጋ እንደሚገኝም ነው ክብርት ሚኒስትር የገለጹት፡፡ በክህሎት ልማት ረገድ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሰጠው ልዩ ትኩረት 7.2 ሚሊዮን ዜጎችን በአጫጭር ስልጠና ማብቃት መቻሉንም ክብርት ሚኒስትር አስረድተዋል፡፡ በልምድ የክህሎት ባለቤት የሆኑ ዜጎችን በማብቃትና እውቅና ለመስጠት የሚያስችል ፕሮግራም በይፋ መጀመሩን የገለፁት ክብርት ሚኒስትር ፕሮግራሙ ‹‹አንድ ሙያ ለአንድ ዜጋ›› በሚል መሪ ቃል ዜጎችን ለማብቃት የተያዘውን ዕቅድ ከማሳካት አንፃርም ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡ የተቋማዊ ግንባታ ሥራውን ጥራት ለማረጋገጥ እንዲቻልም በሚኒስትር መ/ቤቱ ISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራርን ሙሉ በሙሉ ለመተግበር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም በመድረኩ ተብራርቷል፡፡ በዚህ መልኩ የተገኙ ውጤቶችን ለማላቅ የአጋር አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የገለፁት ክብርት ሚኒስትር በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን እየተተገበሩ የሚገኙ ፕሮግራሞችን ከሚኒስትር መ/ቤቱ እሳቤ ጋር የተቀናጀ እንዲሆኑ ለማስቻል ብሎም በተጨማሪ መስኮች ላይ ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top