Mols.gov.et

የብሩህ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር አሸናፊዎች ከችግሮች ውስጥ እድሎችን ፈልቅቀው ማውጣት የቻሉ ናቸው። ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር

June 26, 2023
ከግንቦት 28/2015 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የብሩህ የፈጠራ ሀሳብ ውድድር የአምስት ሺ ዶላር ተሸላሚ የሆኑ 50 አሸናፊዎችን በመለየት ዛሬ ተጠናቋል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በማጠቃለያ ሥነ-ሥርኣቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ‹‹ከህዳር እስክ ህዳር ›› በሚል ስያሜ 3ሺ ሃሳቦችን ለማወዳደር በያዘው ዕቅድ መሰረት 1,137 ሃሳቦችን በመጀመሪያው ዙር ማወዳደሩን ገልፀዋል፡፡ ውድድሩ የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ የፈጠራ ሃሳብ ያለው አቅም በተግባር የታየበት ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ ከውድድሩ የተገኙ ተሞክሮዎች ብዙ ኩባንያዎችን መመስረት፣ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል ያመላከቱ ናቸው ብለዋል፡፡ ለዜጎች ተስፋ፣ ለሀገር አለኝታ የሆኑ ወጣቶች የተሳተፉበት የብሩህ ፈጠራ ውድድር ከበርካታ ችግሮች ውስጥ እድሎችን ፈልቅቆ ማውጣት እንደሚቻል በተግባር የታየበት፣ አካል ጉዳተኝነት የማያግደው ልዩ ችሎታ ደምቆ የተስተዋለበት እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር የቅንጅት ሥራዎችን በማከናወንና የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማትን የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ማዕከል እንዲሆኑ በማስቻል በቀጣይ ጀማሪዎችን ለማበረታታት የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች በሚኒስትር መ/ቤቱ እንደሚተገበሩም ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት አብራርተዋል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶች በማሰባሰብ በአንድ ላይ ስልጠና የሚያገኙበትና የፈጠራ ስራቸውን ወደ ተግባር ቀይረው ወደ ሰፊ ምርት ሂደት እንዲገቡበት የሰመር ካምፕ ፕሮግራም ለመተግበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል አስታውቀዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top