Mols.gov.et

የቤተሰብ ንግድ ቀጣይነት ላለው ሥራ ዕድል ፈጠራ !

April 26, 2024
የቤተሰብ ንግድ ቀጣይነት ላለው ሥራ ዕድል ፈጠራ! በዓለም ላይ”የቤተሰብ ንግድ“ዘላቂ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና ፈጠራን በማበረታታት የሀገራት የኢኮኖሚ ሞተር በመሆን የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡ አሁን ላይ ባደጉት ሀገራት የ”ቤተሰብ ንግድ“ በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላር ገቢ በማመንጨትና ለበርካቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኢኮኖሚ ውስጥ ጫወታ ቀያሪ ከሆኑ ተዋንያን መካከል ተጠቃሹ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እ.አ.አ በ1938 በአነስተኛ የንግድ ድርጅትነት ተመስርቶ ወደ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያነት ያደገውና“በሊ ቤተሰብ” የሚመራው የደቡብ ኮሪያው ሳምሰንግ ኩባንያ ለቤተሰብ ንግድ ውጤታማነት እንደማሳያነት ይቀርባል፡፡ በሀገራችን በቤተሰብ ንግድ ደረጃ ጎልተው የወጡ የንግድ ድርጅቶች ያሉ ቢሆንም በአጠቃላይ በሥራ ዕድል ፈጠራ ስትራቴጂያችን መሰረት የሚፈጠሩት ኢንተርፕራይዞች ዘላቂና ውጤታማ እንዳይሆኑ እንደምክንያት ከሚያነሱት ተግዳሮቶች መካከል የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ችግሮች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ እና መሰል ችግሮች ሳያንበረክካቸው ውጤታማ የሆኑ በርካታ ኢንተርፕራይዞችና የንግድ ድርጅቶች በሀገራችን ይገኛሉ፡፡ ከዚህ አንፃር’አባይነሽ ፋርም’ በግንባር ቀደምነት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ‘አባይነሽ ፋርም’ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካፋ ዞን የቦንጋ ከተማ የሚገኝ ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ማዕከል ነው፡፡ ማዕከሉ በአምስት የቤተሰብ አባላት በቤተሰቡ ቦታ ላይ ሲመሰረት አራት የወተት ላሞችን ብቻ በመያዝ ነበር ሥራ የጀመረው፡፡ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ገዛኸኝ እንደሚገልጹት በ2006 ዓ.ም በአራት የወተት ላሞች የጀመረው ሥራ አሁን ላይ ከ60 በላይ የውጭ ዝርያ ያላቸው ከብቶች ባለቤት ሆኗል፡፡ በዚህም በቦንጋና አከባቢው በቀን በአማካይ 500 ሊትር የወተት ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ ከወተት ምርት አቅርቦት ባሻገር ድርጅቱ የእሴት ሰንሰለትን መሰረት ባደረገ ሥራው የእንስሳት መኖ ዝግጅት፣ አቅርቦት እና የእንስሳት ዘር ማሻሻል ላይ በማተኮር ከራሱ አልፎ ለአካባቢው ህብረተሰብ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ ሳይንሳዊ በሆነው በዚህ የእንስሳት መኖ ዝግጅት፣ አቅርቦት እና የእንስሳት ዘር ማሻሻል ሥራ ድርጅቱ ከአንድ ላም እስከ 45 ሊትር ወተት ማግኘት እንደተቻለ ነው የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ የሚናገሩት፡፡ በርካታ ፈተናዎችን አልፎ አሁን ላይ የደረሰው አባይነሽ ዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ማዕከል በመስኩ በቂ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ62 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለና በክልሉ በአርአያነት የሚጠቀስ ድርጅት ለመሆን ችሏል፡፡ በቀጣይም ሥራውን በማስፋት ከቦንጋ ባለፈ በአጎራባች ወረዳና ዞኖች ጭምር በወተት ምርት፣ በእንስሳት መኖ እና በተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያ አቅርቦት የአከባቢው ህብረተሰብ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በሂደቱ ለበርካቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ያደረገውን ተቋማዊ ሪፎርም ተከትሎ ቀደም ብሎ በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመለየት “ለቤተሰብ ንግድ” ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡
en_USEN
Scroll to Top