Mols.gov.et

”የበለፀጉት መተግበሪያዎች ተገልጋዮች ወደ እኛ እንዲመጡ ሳይሆን አገልግሎቶቻችን ወደ ተገልጋዮች እንዲሄድ የሚያደርጉ ናቸው“ ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር

November 8, 2023
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሦስት የዲጂታል መተግበሪያዎችን አስመርቆ በይፋ ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በተዘጋጀው ይፋዊ የማስመረቂያ መረሃ ግብር ላይ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የክህሎት ልማት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዙና ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ሰፋፊ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ ሥርዓት ውስጥ ከሚካተቱ ከ21 በላይ ስርዓቶችና መተግበሪያዎች 14 ቱ ሠራ ላይ ያዋሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የሦስቱ ይፋዊ ማብሰሪያ ፕሮግራም ተካሂዷል። የዲጂታል መተግበሪያ ስርዓቶቹ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን ወጣቶች የበለፀጉና በኢንተርፕራይዝና ክህሎት ልማት እንዲሁም በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ውስጥ የማይተካ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ የተሰራው ሥራ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ተወዳዳሪ የሚያደርግ፣ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ለማሳካት የሚያግዝ እና ተገልጋዮች ወደ እኛ እንዲመጡ ሳይሆን አገልግሎቶቻችን ወደ ተገልጋዮች እንዲሄድ የሚያደርግና ፍትሃዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ለሥራ ዝግጁ ከተደረጉ መተግበሪያዎች መካከል የተቀናጀ የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ስርዓቱን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ በአጭር ጊዜ መስራቱን የጠቆሙት ክብርት ሚኒስትር ለኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና እና በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የELMIS ፕሮጀክት ጽ/ቤት ለሚገኙ አመራርና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና ዳይሬክተር ክቡር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው ኢንስቲትዩታቸው በአፍሪካ ተወዳዳሪ ተቋም ሆኖ እንዲወጣ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው የበለፀገው ስርዓት በክህሎት ልማት ሥራው ላይ ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ በሀገር ልጆች በልጽገውና ብቃታቸው ተረጋግጦ ለአገልግሎት ዝግጁ የሆኑት ሦስት የዲጂታል ስርዓቶች “ሉሲ” የኢንተርፕራይዞች ግብይት ስርዓት፣ ”የተቀናጀ የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ስርዓት“ እና የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት አካል የሆነው “ብቁ” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ነው፡፡
en_USEN
Scroll to Top