የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት(LMIS) በቢሾፍቱ
October 16, 2023
በሥራ ገበያ መረጃ ሥርአዓት(LMIS) የሚመዘገቡ ዜጎች ቁጥር ከጊዜዳ ጊዜ እያደገ ይገኛል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የዘርፉን መረጃ በተደራጀ መልኩ በማስተዳደር ጥራት ያለውና አስተማማኝ ሀገራዊ መረጃ እንዲኖር በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ የመረጃ ሥርዓት ለመዘርጋት ሰፊ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
በዚህም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓትን(LMIS) በውስጥ አቅም አልምቶ ወደ ሥራ ማስገባቱ ይታወቃል፡፡
በመጀመሪያ ዙር ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከገቡ አካባቢዎች መካከል ብቁ መሆናቸውን የተረጋገጡ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የሉጎ ክፍለ ከተማ ድሬ ነጋ እና የክፍለ ከተማ 2 ኮራ ወረዳ አንድ ማዕከላት ይገኙበታል፡፡
በማዕከላቱ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት(LMIS) ተመዝጋቢዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ የማዕከላቱ የሥራ አስተባባሪዎች እና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ከዕለት ወደ ዕለት የተመዝጋቢ ቁጥር እያደገ መምጣቱ ዜጎች የመረጃ ሥርዓቱ(LMIS) ጠቀሜታ እየተገነዘቡ መምጣታቸው የሚያመለክት መሆኑ የኮራ ወረዳ አንድ ማዕከል የአደረጃጀት ባለሙያ ወ/ሮ ቦካሼ አምሳሉ እና የድሬ ነጋ አንድ ማዕከል ሥራዎች አስተባባሪ አቶ ምትኩ ካሳ ይናገራሉ፡፡
በሁለቱም ማዕከላት ባለፉት ሁለት ወራት የሥራ አጥነት እና የውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ምዝገባ በሥራ ገበያ መረጃ ስርዓቱ(LMIS) እየተከናወነ እንደሚገኝ ከማዕከላቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በሥራ ገበያ መረጃ ስርዓቱ ለመመዝገብ የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ በቅድሚያ በhttps://lmis.gov.et ገብቶ ምዝገባ ማካሄድ ይኖርበታል፡፡ በምዝገባው ወቅት ስርዓቱ በሚሰጠው ሌበር አይዲ መሰረት በአቅራቢያው በሚገኝ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች በመገኘት የባዮ ሜትሪክስ ዳታ መስጠትና ምዝገባውን ማጠናቀቅ ይችላሉ፡፡