የሥራ አውደ ርዕዩ አዳዲስ ተመራቂ ተማሪዎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከማስቻሉ በተጨማሪ የሥራ ገበያውን ፍለጎት የሚረዱበት፣ ክህሎታቸውን ለገበያ የሚያቀርቡበት እና ልምድ የሚቀስሙበት ነው፡፡ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ
October 18, 2023
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከደረጃ ዶት ኮም እና ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በጋራ ያዘጋጁት ሥራ ፈላጊዎች ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የሚገናኙበት ሀገር አቀፍ የሥራ አውደ ርዕይ በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል፡፡
ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በዚህ የሥራ አውደ ርዕይ ከ6000 በላይ የሥራ ዕድች ይፈጠራሉ ተብሏል፡፡
በሥራ አውደ ርዕይ መክፈቻ ላይ የተገኙት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ፤ አዳዲስ ተመራቂዎች የሥራ ዕድል ከማግኘት በተጨማሪ የሥራ ገበያውን ፍላጎት የሚረዱበት፣ ክህሎታቸውን ለገበያ የሚያቀርቡበት እና ልምድ የሚቀስሙበት ነው ብለዋል፡፡
አክለውም ባለፉት አመታት ከደረጃ ዶት ኮም እና ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በተዘጋጁት የሥራ አውደ ርዕይዎች በ100ሺ የሚቆጠሩየሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውን ጠቁመው በዚህ የሥራ አውደ ርዕይ ደግሞ 20ሺህ አዳዲስ ተመራቂ ሥራ ፈለጊዎች እና 3100 የሚሆኑ በደረጃ አካዳሚ የሰለጠኑ ሥራ ፈላጊዎች ከ200 ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ፊት ለፊት የሚገናኙበት የቅጥር ምልመላ እንደሚከናወንበት ገልጸዋል፡፡
የተንከባለሉ የሥራ ዕድሎች እና በየዓመቱ የሚፈጠሩ 2 ሚሊየን የሚሆኑ አዳዲስ ሥራ ፍላጎቶች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታው ይህንን ለማካካስ በሚቀጥሉት 7 ዓመታት ለ20 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
በሥራ አውደ ርዕዩ ከቅጥር ምልመላ ጎን ለጎን “ቅጥር በድጅታል ዘመን” የሚል ርዕስ እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይቶችም ይካሄዳሉ፡፡