Mols.gov.et

NEWS

ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማ በመሆን የህልውና ዘመቻውን ማገዝ እንደሚገባው ተጠቆመ

Nov 16 , 2021 

ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማ በመሆን የህልውና ዘመቻውን ማገዝ እንደሚገባው ተጠቆመ
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ስር ከተደራጁት ተቋማት መካከል የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ እና የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በአገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡
አገራችን አሁን ያለችበትን የህልውና ዘመቻ ሁሉም ዜጋ በእኩል መረዳት እንዲችል እና ለድጋፉም የድርሻውን እንዲወጣ ለማስቻል የተዘጋጀው ይህ የውይት መድረክ ‹‹የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እና የመንግስት ሠራተኛው ሚና›› የሚል አገራዊ መነሻ ሰነድ ለውይት ቀርቦ ውይይት ተካሒዶበታል፡፡
ውይይቱን የመሩት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው ‹‹ኢትዮጵያ ተሸንፋ አታውቅም፤ አሁንም ታሸንፋለች›› ያሉ ሲሆን ለዚህም እንደመንግስት ሰራተኛ ምን ይጠበቅብናል የሚለው ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
‹‹ይህ ጦርነት ተገድደን የገባንት ጦርነት ነው፡፡ የዚህ ጦርነት የኢተዮጵያውያን ዓላማም ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ማቆየት እና ማስቀጠል ነው›› ብለዋል አቶ አሰግድ፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ሠራተኞች አገራችን የገጠማትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በተሰማሩበት ሙያ ተግተው ከመሥራት በተጨማሪ በጦር ግንባር ሔደው እስከመዋጋት ቁርጠኞች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹አገሬ ልጆቼ የሚያድጉባት ናት፤ እኔ የኖርኩባት ናት፤ አገሬ ነጻነቴ ናት ነጻነቴን እፈልጋለሁ አገሬን ለማሳደግ ቁርጠኛ ነን ብለን እንነሳለን›› ያሉት ተሳታፊዎቹ መዝመት የሚችለው ይዘምታል፤ ሌላውም ባለበት ደጀንነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉ ሲሆን ለዚህም በየተሰማራንበት የሥራ መስክ ውጤታማ ሥራ ለመስራት ቁርጠኞች ነን ብለዋል፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ተሻለ በሬቻ በበኩላቸው ‹‹የኢኮኖሚ ጦርነት ፤ የሚዲያ ጦርነት ተከፍቶብናል፡፡ ይህንን ጦርነት ለመቀልበስ ሁላችንም ልንዘጋጅ ይገባል›› ብለዋል፡፡ በቀጣይ የተለያዩ አደረጃጀቶች ተፈጥረው ወደተግባር ለመግባት ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀም ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ሁሉም ዜጋ አካባቢውን በንቃት መከታተል፤ አጠራጣሪ እንቅስቃሴ ሲገኝ ለሚመለከተው የፀጥታ አካል ማሳወቅ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
en_USEN
Scroll to Top