Mols.gov.et

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ከሆኑት ጁሊያ ኔብሌት ጋር ተወያዩ።

June 7, 2023
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአውስትራሊያ ጋር በክህሎት ልማት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ በጋራ ሊሰራ በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያደርግ በኢትዮጵያ በኩል የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ለሥራ ማሰማራትን በተመለከተ ለአምባሳደር ጁሊያ ገለፃ ያደረጉት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው። ለአምባሳደሯ ሲያብራሩም ከኢትዮጵያ ህዝብ 70 ከመቶ ያህሉ ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች መሆኑን በመግለፅ ለሥራ ዝግጁ ለሆነው ወጣት ኃይል የሥራ ዕድል መፍጠር የመንግስት አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል። ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስምምነት በመፈፀም በተለያዩ ሙያዎች የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማሰማራት ጥረት መደረጉን አብራርተዋል። ከዚህ ቀደም በአውስትራሊያ ኤምባሲ ዕገዛ በአፍሪካ ነፃ ቀጠና ዕድል እና ዓለማቀፍ ገበያን መጠቀምን በተመለከተ ለኢንተርፕራይዞች ስልጠና መሰጠቱን ያስታወሱት ክቡር አቶ ንጉሡ ከዚህ ቀደም የተሰጠውን ስልጠና ለማስፋት ውይይት መጀመሩ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም አንስተዋል። የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ለሥራ ማሰማራት፣ በተለዩ ዘርፎች የቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስጠት፣ የኢንተርፕራይዞች ዕድገት፣ የኢትዮጵያ ብየዳ ማዕከል ስልጠና ማስፋት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል። በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ በበኩላቸው በነርሲንግ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና ሌሎችም ዘርፎች የአውስትራሊያን ወቅታዊ ኢኮኖሚ መሠረት ያደረጉ የሥራ ዕድሎችን ለኢትዮጵያውያን ለመፍጠር ውይይቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ብቁ እና የሥራ ልምድ ያለው የሰው ኃይል ለማሰማራት ከመፈለግ ባሻገር በተለያዩ የስልጠና ዘርፎች እና የዕውቀት ሽግግር ላይ በጋራ ለመስራት ውይይቶቹ መጀመራቸውን አድንቀዋል። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከአውስትራሊያ ጋር የልማት እና የትብብር ስምምነቶችን መፈረሟ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመስራት ለተጀመረው ውይይት መልካም አጋጣሚ መሆኑም ተነስቷል።
en_USEN
Scroll to Top