የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ልዩ የክረምት ወራት የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ እና የፈጠራ ሀሳቦች ማሻሻያ መርሀ ግብር ተሳታፊዎችን ጎብኝተዋል፡፡
October 16, 2023
መርሃ ግብሩን የጎበኙቱ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ነቢሃ ሙሃመድ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ተሻለ በሬቻ እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጽ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ መከለያ ባርጊቾ ናቸው።
መርሀ ግብሩ ነሀሴ 9/2015 ዓ.ም የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በይፋ ያስጀመሩት ሲሆን ዓላማውም የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሀሳብ ባለቤቶቹ ዕውቀታቸውን አቀናጅተው ኢትዮጵያን ከሌሎች ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርግ ሥራ የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው።
በዚህም ተሳታፊዎች በእስካሁን ቆይታቸው የግብረ ገብነት፣ የሙያ ስነ-ምግባር እና የሀገር ወዳድነት፣ መፃኢ ጊዜን ብሩህ ማድረግ እንዲሁም ከራስ ባህል እና ማንነት ባሻገር የማመዛዘን ብስለት ላይ ያተኮሩ የማነቃቂያ ስልጠናዎች ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ደግሞ ልምዱና ተሞክሮ ያላቸው የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሰዎች በአካል ተገኝተው ልምድና ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሏቸው ተደርጓል፡፡
በኢንዱስትሪዎች በአካል እየተገኙም የተግባር ልምድና ተሞክሮ እንዲቀስሙ የተደረገ ሲሆን ተሳታፊዎች ያለባቸውን የክህሎት ክፍተት የሚሞላ የተግባር ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።
ልዩ የክረምት ወራት የቴክኖሎጂ ማበልፀጊያ እና የፈጠራ ሀሳቦች ማሻሻያ መርሀ ግብሩ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የተሸጋገረ ሲሆን ወደ ተግባር የሚቀየር የሥራ ፈጠራ ሀሳብ እና ችግር ፈቺና ወደ ገበያ መግባት የሚችል ቴክኖሎጂ በጋራ የሚሰሩ ይሆናል፡፡