Mols.gov.et

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከጣልያን ዓለም አቀፍ ትብብር ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ተግባራዊ የሚያደርገው

May 23, 2024
ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክት ማዕከላቱ የሚሰጡትን አገልግሎት ጥራት የማሻሻልና ተደራሽነታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ተጠቆመ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከጣልያን ዓለም አቀፍ ትብብር ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ተግባራዊ የሚያደርገው የሥራ ገበያ ትስስርና ድጋፍ ፕሮግራም ላይ ውይይት ተደረገ፡፡ ፕሮጀክቱ በቡሬ፣ በቡልቡላ፣ በጅማ እና በይርጋዓለም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዙሪያ በሚገኙ 16 ከተሞች ላይ ለሚኖሩ ዜጎች የእሴት ሰንሰለትን መሰረት ያደረገ የሥራ ዕድል የመፍጠር ዓላማ ያለው ነው፡፡ በዚህም ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረግባቸው የአማራ፣ የሲዳማና የኦሮሚያ ክልሎች ተወካዮችን ጨምሮ ሌሎችም የሚመለከታቸውን አካላት ያካተተው የስትሪንግ ኮሚቴ በፕሮጀክቱ ትግበራ ዙሪያ ውይይት አካሄዷል፡፡ ውይይቱን የመሩት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ በሥራ ሥምሪት አገልግሎት ማዕከላት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ጥራት የማሻሻልና ተደራሽነታቸውን የማስፋፋት ሚና ያለው ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የሥራ ሥምሪት አገልግሎት ማዕከላትን ከቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ፣ ከአግሮ ፕሮሰሰኒግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ከግል ንግድ ድርጅቶች ጋር የሚያስተሳስር ነው ብለዋል፡፡ ስለሆነም ክልሎች መሰል ዓላማ ያላቸውን ፕሮጀክቶች አቀናጅተው በውጤታማነት መምራት እንደሚኖርባቸው ነው ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ያሳሰቡት፡፡ በውይይቱ ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው አካባቢዎች ከኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ጋር በትሥሥር የሚሰሩ ኢንተርፕራይዞችን አቅም ለማጎልበት ፓርኮቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች 16 የሥራ ሥምሪት አገልግሎት(PES) ማዕከላትን የማደስ፣ በግብዓትና ሎጀሲቲክስ የማሟላትና የባለሙያዎችን አቅም የመገንባት እንዲሁም የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓትን(LMIS) ተግባራዊ የሚደረግበትን ሁኔታ በዝርዝር ተመልክተዋል፡፡ የሥራ ገበያ ትስስርና ድጋፍ ፕሮግራሙ ከ11ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
en_USEN
Scroll to Top