Mols.gov.et

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኦማን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር ውይይት አደረገ።

June 5, 2023
ወደ ተለያዩ ሀገራት የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል በመላክ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ የሚገኘው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስምምነቶችን በመፈፀም እየሠራ ይገኛል። ከኦማን የቪዛ፣ የህግ፣ የውጭ ጉዳይ እና ከሠራተኛ ጋር ግንኙነት ያላቸው ኃላፊዎች ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ጋር ተወያይተዋል። የውይይታቸው ዓላማ አዲስ ስምምነት በመፈፀም ለኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠር እና ለኦማንም የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ማቅረብ መሆኑን ክቡር አቶ ንጉሡ ተናግረዋል። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር 77 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አረብኛ ቋንቋን ጨምሮ ሊሠሩ በሚችሉበት ሙያ ለማሰልጠን ዝግጁ መሆናቸውን ያስታወቁት ክቡር አቶ ንጉሡ ኢትዮጵያ የቤት ውስጥ ሠራተኛ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሙያዎች የተመረቁ ባለሙያዎችን ለዓለም አቀፉ የሥራ ገበያ ለማቅረብ እየሠራች ነው ብለዋል። ኦማን መብታቸውን አስጠብቃ የምታሠራቸው ሠራተኞችን እንደምትፈልግ እና ለዚህም የቀድሞውን ስምምነት ማደስ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ማዘጋጀታቸውን የኦማን የሠራተኛ ጉዳይ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ገልፀዋል። ክቡር አቶ ንጉሡ እንደገለፁት የምንልካቸው ዜጎች መብታቸው እንዲጠበቅ ስለምንፈልግ ረቂቅ ሰነዱን የህግ ባለሙያዎች በጥልቀት እንዲመለከቱት በማድረግ ሃሳብ የሚሰጥበት እና በኤምባሲዎች በኩል የሚፈፀም ይሆናል ብለዋል። ከኦማን የመጡት የሥራ ኃላፊዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ያበለፀገውን የመረጃ ስርዓት በተመለከተ ገለፃ የተደረገላቸው ሲሆን ለዚሁ ስራ የተመቻቸውን እና ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኘውን ቢሮ ጎብኝተዋል።
en_USEN
Scroll to Top