የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከልና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር
December 11, 2024

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከልና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለዜጎች ሰፊ ሥራ ዕድልን ለመፍጠር በሚያስችሉ አማራጮች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ባስተላለፉት መልዕክት ዲጂታል ኢኮኖሚን በመጠቀም ዘላቂ ልማትንና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሀገራችን ‹‹ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025›› ግብን ቀርፃ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች ብለዋል፡፡
የዲጂታላይዜሽን ሥርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ የዜጎችን ተወዳዳሪነት ለማጎልበት ያለውን አስተዋፅኦ መነሻ በማድረግ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የዲጂታል ኢንተርፕሪነርሺፕ እንቅስቃሴን መጀመሩን የገለፁት ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ባለማው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት አማካኝነት ቁጥራቸው ከ26ሺ ለሚልቁ ዜጎች የርቀት ሥራ(remote job) መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2023 የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሰዎች ከሀገራቸው ሳይወጡ በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የሥራ መስኮች ላይ መሰማራት በሚያስችለው የአውትሶርሲንግ ቢዝነስ ከ1.2 ትሪሊዮን ዶላር በላይ መንቀሳቀሱ ዘርፉ ዜጎችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ያለውን አቅም የሚያመላክት መሆኑም ተብራርቷል፡፡
ዘርፉ አዲስ እንደመሆኑ በሚጠበቀው ደረጃ ዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀትና የአሠራር ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ምህዳሩን ምቹ ከማድረግ አንፃር የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ ኢንተርፕረነሮችና ወጣቶችን ከአሠሪዎች የሚያግናኙ የቴክኖሎጂ ፕላትፎርም አልሚዎች ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን በጊግ ኢኮኖሚ የቁርጥ ሥራ እና ፍሪላንሲንግ ኢንዱስትሪ ላይ በሚያተኩሩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡


