Mols.gov.et

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አገልግሎቱን ለማዘመን ያደረገውን ዝግጅት ለተለያዩ ዘርፎች የክልል አመራሮች አስጎበኘ።

July 7, 2022
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አመራሮች ተቋሙ የዘመኑን ቴክኖሎጂ ታሳቢ በማድረግ ለአገልግሎት ምቹ የሆነውን ህንፃ እና ያበለፀጋቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለክልል አመራሮች እና ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎች አስጎብኝቷል። በአዲስ አበባ በተለምዶ ላምበረት በሚባለው አካባቢ ከዚህ ቀደም ቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ ሲገለገልበት የነበረውን ሕንፃ ለሥራው በሚመች መልኩ መዘጋጀቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል የገለፁ ሲሆን ቦታው ዘመናዊ የቢሮ አስተሳሰብን የያዘ እና ደረጃውን ለጠበቀ የቢሮ አደረጃጀት ምቹ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አዲሱ ሕንፃ አገር በቀል ቁሳቁሶችን እና የወጣቶችን ፈጠራ በመጠቀም የሥራ ባህል ማዳበርን እና የክህሎት ፅንሰ ሃሳብን በማጎልበት መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል ፡፡ ምርታማነትን እና ፈጠራን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀው የህንፃው ይዘት ዓለም ከደረሰበት ቴክኖሎጂ አኳያ የተደራጀ እንዲሁም ግልፅነት የተላበሰ መሆኑ ለሠራተኛውም ሆነ ለተገልጋዩ እርካታ የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የበለጸጉት የቴክኖሎጂ ውጤቶችም ተቋሙን ከማስተዋወቅ ባሻገር ለውስጥም ሆነ ለውጭ ተገልጋይ በቀላሉ መገናኘት እና ጉዳይን መፈፀም የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የክልል ቢሮ ኃላፊዎቹ እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮቹ ላምበረት ከሚገኘው ዋናው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሕንፃ ባሻገር የሠራተኛ ዘርፍ አገልግሎት የሚሰጥበትን እና እንደ አዲስ እየተገነባ የሚገኘውን ጊቢ ጎብኝተዋል፡፡ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አሰግድ ጌታቸው እየተገነባ የሚገኘው ቢሮዎችን ከቴክኖሎጂ ያቀናጀ እና ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን የሚፈታ ቴክኖሎጂን ያጣመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለኤጀንሲዎችም ሆነ ወደተለያዩ አገራት ለሚደረግ ጉዞ ይፈጅ የነበረውን 30 ቀን ወደ 15 ቀን ለማምጣት የአሰራር ለውጦችንም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top