Mols.gov.et

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሴቶች ፎረም መደበኛ ሥብሰባ ተካሄደ

November 23, 2023
ሴት ሠራተኞች ያላቸውን እውቀትና ብቃት በጋራ በማቀናጀት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ የማስቻል ዓላማን በመያዝ ነበር የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሴት ሠራተኞች ፎረም ህዳር/2015 ዓ.ም የተመሰረተው፡፡ ፎረሙ ከምስረታው ጀምሮ እያከናወናቸው በሚገኙ ተግባራትና በቀጣይ በያዛቸው ዕቅዶች ላይ የሚመክር መደበኛ ስብሰባ አካሄዷል፡፡ በስብሰባው መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት የሚኒስትር ፅ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ መከለያ በርጌቾ ፎረሙ ሴቶች እርስበእርስ የሚማማሩበት፣ የሚመካከሩበት፣ ሃሳብና ተሞክሮ የሚለዋወጡበት መድረክ ሆኖ የሚያገለግል በመሆኑ አደረጃጀቱን ተጠቅሞ ውጤታማ ተግባር ማከናወን ይገባል ብለዋል፡፡ መሰባሰብና መደራጀት ወደ መብቃት የሚወስድ አንድ አቅም ነው በማለት የገለፁት ወ/ሮ መከለያ በቀጣይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስፈፃሚና ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ አገር አቀፍ የሴቶች ፎረም ለመመስረት በሚኒስቴር መ/ቤቱ ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡ ፎረሙ ሴቶችን በማብቃት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት የሚያስችል አቅምን የመፍጠር ዓላማ ያለው መሆኑን የገለፁት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ እርቅነሽ ዮሃንስ አዳዲስና ጉልበታም የሆኑ ሃሳቦችን በማዋጣት ፎረሙን የማጠናከር ሥራ ከሁሉም አባላት የሚጠበቅ ነው ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በመድረኩ ‹‹የራስን ሀብት መፈለግ›› በሚል ርዕስ ዕምቅ አቅምን በመፈተሸና በመጠቀም ላይ ያተኮረ ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን በፎረሙ ዕቅድ አፈፃፀምና ቀጣይ እቅዶችም ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡
en_USEN
Scroll to Top