Mols.gov.et

የምንከተለው አቅጣጫ የክልሉን ህዝብ ምርታማነት ለመጨመር የሚያስችል የክህሎት ልማትን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው። ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል

May 23, 2023
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በቀጣይ ወራት ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ልዩ የንቅናቄ ዕቅዱ ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በአሶሳ ተወያየ። በመድረኩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አሻድሊ ሀሰንን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል። ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ልዩ የንቅናቄ ዕቅዱን ያቀረቡት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል እንደገለጹት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክህሎት ልማቱና ሥራ ዕድል ፈጠራው መስክ አበረታች ውጤት የተገኘ ቢሆንም ካለው ሀገራዊ ፍላጎት አንፃር የሚቀሩ ነገሮች አሉ። ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ቢሆንም ይህንን ፀጋ አልምቶ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግና የክልሉ ልማት ማሳለጥ በሚያስችል መልኩ ጥቅም ላይ አልዋለም። ስለሆነም ከችግሩ የቀደመ ምላሽ ለመስጠት በግዜ የለንም መንፈስ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅዱን ለማሳካት በየደረጃው የሚገኝ ሁሉም አመራር ተሰናስሎ መረባረብ ይኖርበታል። ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ እሴት በማከል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እና የክልሉን ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በአካባቢ ፀጋ መለየትና ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ የምንከተለው አቅጣጫ የክልሉን ህዝብ ምርታማነት ለመጨመር የሚያስችል የክህሎት ልማትን መሠረት ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው ብለዋል። በዚህ ላይ በመመስረት የየዘርፉን ዕቅድ ሸንሽነን መስራት ከቻልን የክልሉን ትራንስፎርሜሽን በማረጋገጥ ረገድ ሊታይና ሊቆጠር የሚችል ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያመላከቱት ክብርት ሚኒስትር ጊዜ የሚፈልጉት ላይ ደግሞ መሰረት የሚጣልበት ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው እንደገለፁት፣ የክህሎት ልማት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ የአንድ ሴክተር ተግባር አይደለም፡፡ ጉዳዩ ከድህነት የመውጣትና ልማትን በቀጣይነት የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ እንደ ክልል ዘርፉ በምክትል ርዕሰ- መስተዳድሩ እንዲመራና አደረጃጀቱም እንዲስተካከል የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡ ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ መሆኑ፣ ቁጭት የፈጠረ አመራር መኖሩ እና መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ልዩ ትኩረት እንደ ክልል የታሰበውን ዕቅድ ለማሳካት አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያወሱት ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሥራ ባህል ጋር ተያይዞ የባህሪ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎች ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top