Mols.gov.et

የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት በክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና…

February 3, 2024
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት በክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሰላማዊ ኢንዱስትሪ ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ “ውጤታማ ተግባቦት ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሀሳብ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት የጋራ ጉባኤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሪፎርም ሀሳቦችና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚያተኩር ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የክህሎት ልማት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሰላማዊ ኢንዱስትሪ የመፍጠር ሥራ የአንድ ሴክተር ጉዳይ አይደለም፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብቁና ተወዳዳሪ የሰለጠነ የሰው ሃይል የማፍራት፣ የማክሮ ኢኮኖሚው ትልቅ ስብራት የሆነውን የሥራ አጥነት ችግር ትርጉም ባለው መልኩ የመቀነስ እና ምርታማነትን ማዕከል ያደረገ የኢንዱስትሪ ግንኙነት የመፍጠር ተልዕኮ አለው፡፡ ይህም በትኩረት ከሰራንበት የትላንት የተከማቸ ዕዳን የሚመልስ፣ የዛሬ ዕድላችንን የሚወስን እና የነገ ተስፋችንን ብሩህ ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ስለሆነም እንደ ሀገር ሁለንተናዊ ልማትና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተቀመጠው ግብ እንዲሳካ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ በተለመደው አካሄድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እንደማይቻል ከግምት በማስገባት ሁሉም በትልቁ አቅዶ በትልቁ መፈፀም የምርጫሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል፡፡ ስለሆነም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት በክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሰላማዊ ኢንዱስትሪ ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ ያላቸው ሚና የማይተካ መሆኑን የገለጹት ክብርት ሚኒስትር የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አካላት በዘርፉ የጋራ መግባባት መፍጠር እና የባህሪ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎችን በመስራት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ አምስቱን የኢኮኖሚ የትኩረት መስኮች ላይ የሚያጠነጥኑ ሥራዎችን መስራት ይኖርበታል፡፡ ሃገራዊ ልማትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዓላማን በአግባቡ በመረዳት በሚዲያና ኮሙኒኬሽን እቅድ ውስጥ አካቶ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top