Mols.gov.et

የመጀመሪያው የአፍሪካ የሥራ ጉባዔ ሊካሄድ ነው።

July 4, 2023
የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኝ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚሰሩ አካላት ቅንጅት እንዲጠናከርና በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በቀላሉ ለመለየትና መፍትሄ ለመስጠት እንዲሁም አዳዲስ አሰራሮችን መላመድ እንዲቻል በር እንደሚከፍት የተገለፀው ሀገራዊ የሥራ ዕድል ጉባዔ በዚህ ዓመት በአህጉር ደረጃ እንደሚካሄድ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ገልፀዋል። አስቀድመው በተዘጋጁት ሁለት የሥራ ጉባዔዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች ወደ አህጉር አቀፍ ደረጃ ማሳደግ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው በመታመኑ ዘንድሮ ጉባኤው ለመጀመሪያ ጊዜ “ምቹና ዘላቂ ሥራ ለአፍሪካ ብልፅግና!” በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ደረጃ ከሰኔ 30 እስከ ሀምሌ 2/2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ ይሆናል ብለዋል። ክቡር አቶ ንጉሡ የአህጉር አቀፍ ጉባዔው ዋና ዋና ዓላማዎችን ሲዘረዝሩ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር አንድ መንገድ እንዲሆን ማስቻል፤ በአፍሪካ የሚገኙ ሥራ ፈጣሪዎች እና በኢንተርፕርነርሽፕ ስነ ምህዳሩ ያሉ አካላት ትስስር እንዲፈጥሩ ዕድል መፍጠር፤ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር የአፍሪካ ሃገራት ባሏቸው ፖሊሲዎች ዙሪያ ልምድ መለዋወጥ እንዲችሉ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። በጉባዔው የአፍሪካ ሀገራት ተወካዮች የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች፣ በክህሎት ልማት እና ሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ የሚደረጉ የፓናል ውይይቶች፣ የሚዲያ ገለፃዎች፣ ኤግዚቢሽኖች፣ በዘርፉ የላቀ አፈፃፀም ላላቸው አካላት እውቅና የሚሰጥባቸው ሥነ-ሥርዓቶች ይከናወናሉ፡፡ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች፣ የኢትዮጵያ የክልል አመራሮች፣ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ተቋማት፣ የልማት አጋር አካላት፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ የቴክኖሎጂ መሪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የስብሰባው ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡ AeTrade Group ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉዓለም ስዩም በበኩላቸው በአህጉሪቱ እያደገ ለመጣውን የወጣቶች ቁጥር የሥራ ዕድል መፍጠር እንዲቻል ጉባኤው ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመው ጉባኤወን ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጋር በመተባበር በማዘጋጀቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top