ዜጎች መብታቸው ተጠብቆ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ሌሎች ሀገራት እንዲጓዙ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል
December 18, 2024

ዜጎች መብታቸው ተጠብቆ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ሌሎች ሀገራት እንዲጓዙ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ቀን “ህጋዊ መንገድን እናበረታታ” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በአዲስ አበባ ተከብሯል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ዳንኤል ተሬሳ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በሕገ-ወጥ መንገድ የሚከናወን ስደት በዜጎች ላይ የተለያዩ አደጋዎችን እያደረሰ ይገኛል፡፡
ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ውጭ የሚያደርጉት ጉዞ በሕገ ወጥ ስደት የሚደርስባቸውን እንግልት ከመቀነስ በተጨማሪ በላኪና በተቀባይ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር በመሆኑ በትኩረት እየተሰራበት ነው።
መንግሥት ዜጎች በአስተማማኝ እና በሕጋዊ መንገድ ወደ የተለያዩ ሀገራት እንዲጓዙ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በዚህም ዜጎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ከመመልመል አንስቶ የሥራ ላይ ሥልጠና በመስጠት ብቁ በማድረግ ወደ ውጭ ሀገራት እንዲጎዙ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል፡፡
መንግስት ዜጎች በሄዱበት ሀገር ክብራቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ከአጋር አካላት ጋር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ሚኒስቴር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት ዋና ተጠሪ አቡባቱ ዋኔ በበኩላቸው ስደተኞች በሕጋዊ መንገድ ወደ የተለያዩ ሀገራት መጓዛቸው ዘላቂ እድገት ለማምጣት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በሕጋዊ መንገድ የሚደረግ ጉዞ ስደተኞች መብታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲሁም ተረጋግተው ሥራቸውን እንዲሰሩ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
ሀገራት ዜጎቻቸው በህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲጠቀሙ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው አሳስበው አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ለውጤታማነቱ በጋራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ ህገ ወጥ ስደትን በመከላከል ህጋዊ ስደትን ለማበረታታት እያከናወነችው ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጋራ እንደሚሰራ መገለፁን ኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።


