ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የባዮሜትሪክ መረጃ መሰብሰቢያ እና የ ICT ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ፡፡
June 7, 2023
በርክክብ ስነ-ስርአቱ ላይ ከተበረከቱ እቃዎች ውስጥ የባዮ ሜትሪክ መረጃ መሰብሰቢያ ኪቶች፣ ኮምፒውተሮች፣ ታብሌቶች፣ ላፕቶፖችና ካሜራዎች ይገኙበታል፡፡
ይህ ድጋፍም በሁለቱም ተቋማት እና በምስራቅ አፍሪካ አገራት ያለውን ፍልሰት አስተዳደር ለማሻሻል የጀመሩትን ሥራዎችና በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በርክክቡ ወቅት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አሰግድ ጌታቸው እንደገለፁት ተቋሙ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያካሄዳቸውን የሪፎርም ሥራዎች ለማገዝ እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ ነው፡፡
በከተቋሙ የተገኙ የቁሳቁስ ድጋፎች በቀጠናው ያለውን የሥራ ፍሰትን ከማሳለጥና ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮችን ከመቅረፍ አንፃር ጉልህ እገዛ ያደርጋል፡፡
‹‹ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን አገር አቀፍ የሰራተኛ ገበያ መረጃ ስርዓት ለመዘርጋት ሰፊ ስራ ሲሰራ ቆይቷል›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በድጋፍ የተገኙት ቁሳቁሶች ከዚህ በፊት በሚኒስቴር መ/ቤቱ የተገዙትን ጨምሮ በመላ አገሪቱ በሚገኙ የሥራ ማዕከላት አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥሩም አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ የአለም አቀፉ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የአፍሪካ ህብረትና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ልዩ ተወካይ ሚስተር አሌክሶ ሙሴንዶ ከአፍሪካ አህጉር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በስደት ወደሌሎች የአለማችን ክፍሎች ስራ ፍለጋ ይሄዳሉ ሆኖም ግን የት እንደደረሱ፣ ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ፣ እነማን እንደሆኑ እና ከራሳቸውስ አልፈው ለአገራቸው ምን አበረከቱ ስለሚለው መረጃ የለንም፡፡
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የበለጸገው ሲስተም ይህንን መሰረታዊ ችግር የሚቀርፍ በመሆኑና ይህን ጅምር ለማጎልበትም ድጋፍ ማድረግ መቻላቸው ደስታን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡