Mols.gov.et

ውበት፣ ምቾትና ቀልጣፋ አገልግሎት መገለጫው የሆነ ማዕከል

October 8, 2025
ውበት፣ ምቾትና ቀልጣፋ አገልግሎት መገለጫው የሆነ ማዕከል ‹‹አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት›› በአዲስ አበባ ከተማ፣ መሃል አራት ኪሎ ፣ አራዳ ክፍለ ከተማ ህንፃ ላይ ይገኛል፡፡ የህንፃውን የመግቢያ በር አልፈው ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ከፊት ለፊትዎ አምሮ በተሠራ እንግዳ መቀበያ ላይ የተቀመmች ትሁት አስተናጋጅ ‹‹ እንኳን ደህና መጡ›› ብላ በትህትና የተሞላ ፈገግታ ትቸርዎታለች፡፡ ይህ ስፍራ አንድም ስለሚፈልጉት አገልግሎት መረጃ የሚያገኙበት ሲሆን አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶች ስካን ተደርገውና ወደ ዲጂታል መረጃነት ተለውጠው ወደ አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎች የሚላክበት ነው፡፡ በመረጃ ዴስክ ላይ ያለዎትን ቆይታ ሲያጠናቅቁ በስተቀኝዎ ወደሚገኘው አዳራሽ ያመራሉ፡፡ በዚህ ክፍል አይን በሚስብ ዲዛይን የተሰሩ ባለጉዳይ የሚስተናገድባቸው መስኮቶች ይመለከታሉ፡፡ ከመስኮቶቹ ጀርባ ደረጃውን የጠበቀ የደንብ ልብስ የለበሱና በትህትና የተሞሉ ባለሙያዎች የሚፈልጉትን አገልግሎት በፍጥነትና በቅልጥፍና ሊሰጥዎት በተጠንቀቅ ይጠብቅዎታል፡፡ እያንዳንዱ ባለሙያ ከተቀመጠበት ወንበር በላይ ማንነቱን፣ የየትኛውን ተቋም አገልግሎት እንደሚሰጥና ፎቶውን ጭምር የያዘ ዲጂታል ስክሪን ይታያል፡፡ የክፍሉ ዲዛይን ፣ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶቹ የተላበሱት ፀአዳ ቀለም ንፁህና ምቹ የሆነ ስሜትን ያላብስዎታል፡፡ የማዕከሉ የአገልግሎት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ማስረሻ እንደሚገልፁት በማዕከሉ በርካታ የተገልጋይ ቁጥር የሚያስተናግዱ በ13 ተቋማት ውስጥ የነበሩ 107 አገልግሎቶች ዲጂታል ስርዓትን በመጠቀም በፍጥነትና በቅልጥፍና አገልግሎት እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ በህንፃው አራት ወለሎች ላይ በተመሳሳይ መልኩ የተደራጀው ማዕከል በውስጡ የኢኮኖሚ፣የመሬትና የመሬት ግንባታ፣ እንዲሁም የቤቶች አገልግሎቶችን አካትቶ ይዟል፡፡ ማዕከሉ ራሱን የቻለ የዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ያለው ሲሆን አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሶፍትዌሮችን እና የኔትዎርክ መሰረተ ልማትን ይከታተላል፡፡ አጠቃላይ በማዕከሉ በሚሰጠው አገልግሎት ውስጥ የዲጂታል መረጃ ፍሰትን ይቆጣጠራል፡፡ የተቋሙን የሳይበር ደህንነት ላይ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግ መሆኑ አገልግሎቱ ደህንነት የተረጋገጠ እንዲሆን ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ያለምንም መቆራረጥ እንዲሰጥ ራሱን የቻለ የጀነሬተርና ዩፒኤስን ጨምሮ ዘመናዊ የሆነ የኃይል አቅርቦት ሥርዓት የተሟላለት መሆኑንም አቶ ቴዎድሮስ ይገልፃሉ፡፡ ቅልጥፍና እና ፍጥነት የተቋሙ አገልግሎት አሰጣጥ ዋንኛ መገለጫ እንደመሆኑ የማዕከሉ አገልግሎት አሰጣጥ የራሱ የሆነ የአሠራርና ስታንዳርድ እንደተዘጋጀለትም አቶ ቴዎድሮስ ይናገራሉ፡፡ እያንዳንዱ ባለሙያ ከደንብ ልብስ አጠቃቀም ጀምሮ አገልግሎት የሚሰጥበትና ለእንግዶች የሚያሳየው ባህሪ ጭምር በስታንዳርዱ ውስጥ ተካቷል፡፡ በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሥራና ክህሎት ዘርፍ 3 አገልግሎቶችና 10 ተግባራት ይሰጣሉ፡፡ ሥራ ፈላጊ ግንዛቤ ማደራጀት፣ የሀገር ውስጥ ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ቁጥጥር እና ለሥራ ፈላጊዎች መንግስታዊ ድጋፎችን በተገቢው መልኩ ማመቻቸት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ አገልግሎቶቹ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በለማው የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (LMIS) የሚሰጡ መሆናቸው ከዚህ ቀደም ተደራጅቶ ወደ ሥራ ለመግባት የሚወስደውን ረጅም ጊዜና እጅግ የተንዛዛ አሰራር መቀየር ተችሏል፡፡ የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ አቋቁመውና ተደራጅተው ለመስራት የሚፈልጉ ወጣቶች አስፈላጊ የሆነውን ሰነድ ሙሉ በሙሉ አሟልተው ወደ ማዕከሉ ከመጡ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ጉዳያቸውን ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ ኢንተርፕራይዝ በማቋቋም ሂደት አስፈላጊ የሆኑ የፈቃድ ምዝገባ፣ የስም ስያሜ፣ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የመሳሪያ ሊዝና የዘርፍ ማህበራት ማደራጃ አገልግሎት በማዕከሉ ውስጥ በተሟላ መልኩ መገኘቱ ለገልግሎቱ በሚፈለገው ደረጃ ፍጥነትንና ቅልጥፍናን እንዲላበስ አስችሎታል፡፡ የመሶብ አንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎትን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በማስፋፋት መንግስታዊ አገልግሎቶችን ምቹና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ ተደራሽ የማድረግ ጥረቱ ቀጥሏል፡፡ እርስዎም በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት መስጫ ማዕከል የነበርዎትን ቆይታ አጠናቀው ሲወጡ ውብና ምቹ በሆነ ቦታ፣ ተገቢው ክብር ተቸርዎት የሚፈልጉትን ማግኘት ችለዋልና ‹‹መሶብ ማለት ውበትና ምቾት ነው፡፡›› ብለው ቢያስቡ የሚገርም አይሆንም፡፡ ብቃትን፣ ትህትናን እና ስነምግባርን በተላበሱ ባለሙያዎች የተሰጥዎትን አገልግሎት በማሰብ ‹‹መሶብ ማለት ጥራት ያለው አገልግሎት ነው›› ከሚል ድምዳሜ ላይ ቢደርሱም አልተሳሳቱም፡፡ ግዜዎን ቆጥበውና በአገልግሎቱ ረክተው በመውጣትዎ ‹‹መሶብ የሀገራችንን የመንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርድ በእጅጉ ልቆ የታየበት ማዕከል ነው›› ብለው ቢመሰክሩም ፍፁም ትክክል ነዎት!
en_USEN
Scroll to Top