እጀ ወርቆች፣ ባለ ብሩህ አእምሮዎችና ልቦናዎች እንኳን ደስ አላችሁ !!
August 27, 2023
በቴክኒክና ሞያ ስልጠና ታሪክ በዘርፉ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የምረቃ ስነ-ስርዓት በዛሬው ዕለት በሥራና ክህሎት ተጠሪ ተቋም በሆነው የቴክኒክና ሞያ ኢንስቲትዩት በ6 ፋካሊቲ መካኒካል ቴክኖሎጂ ፣ ሲቪል ቴክኖሎጂ፣ ኤሌክትሪካል ኤሌክትሮኒክስ ፣ አይሲቲ ፣ ቴክስታይልና ጋርመንት እንዲሁም በአግሮ ፕሮሰሲንግ በማትሪክ ውጤታቸው ከፍተኛ ውጤት አምጥተው የነበሩ ተማሪዎችን ተቀብሎ አሰልጥኖ ለምረቃ አብቅቷል።
ከዚህ ከቀደም የምናውቀው ወደ ቴክኒክ እና ሞያ ስልጠና ማዕከል የሚቀላቀሉ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ያላመጡ እንደነበረ ይታወሳል። አሁን ግን በተሻለ እና በከፍተኛ ውጤት የመግቢያ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ሞያዊ ክህሎትን በጥራትና በተሻለ ፈጠራ ወደ ተግባር ለመቀየር ተቀላቅለው ዛሬ ለምርቃት ቀናቸው ደርሰዋል።
በዘርፉ ቀጠናዊ ትስስርን ለማጠናከር ያለመ ሁለት የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ዜጎች በዛሬው ዕለት የተመረቁ ሲሆን እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ በዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጾ ላበረከቱ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷል።
በመደበኛ የመማር ማስተማር ስርዓትም ውስጥ ከማለፋቸው በላይ የሞያ ፈተናውንም በተግባር ጥንቅቅ አድርገው ብቃታቸው እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ የቀረቡ ተመራቂዎቻችን ለነገይቱ በራሷ ምርት ለምትኮራው የራሷን ብራንድ በዓለም ተወዳዳሪ ለምታደርገው ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋዎች ናቸው።
በዛሬው እለት በቴክኒክና ሞያ ኢንስቲቲውት የተመረቁት ተማሪዎችም በቅድመ-ምረቃ በመጀመሪያ ዲግሪ (Level 6) እና በድህረ-ምረቃ በማስተርስ (Level 7) በድምሩ 3600 በላይ እጩ ምሩቃን ተመርቀዋል።
እንኳን ደስ አላችሁ ! እኛም በስልጠና ማዕከሉም ሆነ በተመራቂዎቹ የአዲስ ምዕራፍ ጉዞ በእጅጉ ደስ ብሎናል።