Mols.gov.et

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሥራ ጉባዔን ልታካሂድ ነው

June 4, 2023
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በየዓመቱ የሚያካሂደው ብሔራዊ የሥራ ጉባዔ በዚህ ዓመት በአፍሪካ ደረጃ ሊካሄድ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከአንድ ወር በኋላ የሚካሂደውን የሥራ ጉባዔ በተመለከተ ለአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት አምባሳደሮች ገለፃ ተደርጓል። አፍሪካ አብዛኛው የህዝብ ቁጥሯ ወጣት መሆኑን እና ለዚህም የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ሀገራት ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል ያሉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው። በንግግራቸው ጉባዔው በአፍሪካ ደረጃ መዘጋጀቱ በአህጉሪቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር ሂደት አስቸጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ በጋራ ለመስራት ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል። የአፍሪካ ህብረት አፍሪካ የነፃ ንግድ ቀጠናን መርህ አጀንዳ ባደረገበት ወቅት ጉባዔው በጋራ መዘጋጀቱ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ያነሱት ክቡር አቶ ንጉሡ የኢትዮጵያ መንግስት በሥራና ክህሎት መሪነት የአፍሪካ የሥራ ጉባዔ እንዲዘጋጅ ሲያደርግ በአባል ሀገራት መካከል ጥምረት በመፍጠር አህጉሪቱ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ኮንስትራክሽን እና ሌሎችም ዘርፎች የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች እንዲጨምሩ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንን ወክለው ንግግር ያደረጉት አንቶኒዮ ፔርዶ ምቹና ዘላቂ የሥራ ዕድል ለአፍሪካውያን ለመፍጠር ፖሊሲዎችን ማሻሻል እና ብዙ ወጣቶችን የሚያሳትፉ አዳዲስ የሥራ መስኮችን ማስፋት እና ክህሎትን የማሳደግን አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥተውታል። የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ አፍሪካ ህብረት እና ኤ.ኢ ትሬድ ግሩፕ በጋራ በሚያዘጋጁት በዚህ ጉባዔ የፓናል ውይይቶች እና የተለያዩ ዝግጅቶች የሚካተቱበት ሲሆን የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ልምዳቸውን እንደሚያቀርቡበት ይጠበቃል።
en_USEN
Scroll to Top