አፍሪካ ያልተነካ እምቅ አቅም እና ሀብቷን በመጠቀም የኢኮኖሚ ነጻነቷን እንድታረጋግጥ መስራት ይገባል፡፡ ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
July 7, 2023
የአፍሪካ የሥራ ፈጠራ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
“በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ገበያ የሥራ ፈጠራ፣ የዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነትን ማፋጠን” በሚል መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ በሚገኘው ፎረም የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ንግግር አድርገዋል፡፡
በዚህም ክህሎት ጥራት ላለው የሥራ ዕድል ወሳኝ በመሆኑ መንግስት ክህሎት ላይ ትኩረት በማድረግ የሥራ እድል ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አፍሪካ ያልተነካ እምቅ አቅም እና ሀብቷን በመጠቀም የኢኮኖሚ ነጻነቷን እንድታረጋግጥ መስራት ይገባናል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ትልቁ አጀንዳ የሥራ ዕድል ፈጠራ ነው ያሉት ክብርት ሚኒስትር የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና እንዲመሰረት የተደረሰው ስምምነትም በአህጉሪቱ ሰፊ የሥራ እድል እንዲፈጠር በር የሚከፍት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ፎረሙ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የዲጂታል እና የፋይናንስ አካታችነትን ትግበራ፣ ለአፍሪካ ወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ እና የአፍሪካ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት ጥምረት ፍኖተ ካርታ ላይ ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም ጋር ተያይዞ የአፍሪካ ትስስር ቀን በመከበር ላይ ይገኛል።
በመድረኩ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረት የንግድ፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና ማዕድን ኮሚሽነር አልበርት ሙቻንጋ፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ሞኒክ ንሳንዛባንጋዋ፣ የአፍሪካ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ተቋማት አመራሮች እና የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ተገኝተዋል።