Mols.gov.et

አዲሱ የዘርፉ እሳቤ የታደገው ተቋም

January 28, 2026
አዲሱ የዘርፉ እሳቤ የታደገው ተቋም ከዓመታት በፊት ባሳየው ዝቅተኛ አፈፃፀም ለመዘጋት ከጫፍ ደርሶ ነበር፡፡ የሚጠበቅበትን ብቃት ማረጋገጥ ባለመቻሉም አሰልጣኞችም ሆነ ሰልጣኞች በእጅጉ ተስፋ የቆረጡበትን ጊዜም አሳልፏል፤ የአሶሳ ፖሊቴክኒክ ኮለጅ! በተቋሙ አስተዳደር ላይ በተደረጉ ለውጦችና በተሠሩ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎች ከነበረበት ችግር እንዲያገግም ማድረጉን የኮሌጁ ዲን አቶ ተመስገን ሀይሉ ይናገራሉ፡፡ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተቀርፆ ወደ ሥራ የገባው የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ አዲስ አሳቤ ደግሞ ኮሌጁን ለዓመታት የተጫነውን ችግር ፈንቅሎ ለመውጣት ያስቻለው ብርቱ አቅም ሆኖታል፡፡ ዕቅዱን እንደ አዲስ መከለስ ኮሌጁ እሳቤውን ለመተግበር የወሰደው ቀዳሚ እርምጃ ነበር፡፡ ኮሌጁን ለአሰልጣኝ መምህራንና ለሰልጣኞች ምቹ የማድረግ ብሎም ወርክሾፖቹን የማጠናከር ሥራ ጎን ለጎን ተከናወኗል፡፡ አዳዲስ ሃሳብ ያላቸው ሰልጣኞች ሃሳቦቻቸውን የሚያሳድጉበት፣ የሚያጎለብቱበትና ወደ ተግባር የሚቀይሩበት የኢንኩቤሽን ማዕከልም በኮሌጁ ተቋቁሟል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን የኩባንያዎች መፈልፈያ ማድረግ የአዲሱ የዘርፉ እሳቤ አንዱ ዘረመል መሆኑን መነሻ በማድረግ ኮሌጁ ያለውን አቅም ተጠቅሞ ወደ ምርት ገብቷል፡፡ በዚሁ መሰረት ለአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት የሚሆን ቴራዞ እያመረተ በማቅረብ 17 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችሏል፡፡ የገጠር ሞዴል መንደሮች ግንባታ የሚውሉ 2መቶ ሺ ጡቦችን እንዲያመርት በክልሉ መንግስት በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ የኮሌጁ ዲን አቶ ተመስገን ሀይሉ ይገልፃሉ፡፡ በምርት ሂደቱ ላይ መደበኛና የአጭር ጊዜ ሰልጣኞች እንዲሳተፉ መደረጉም የተሟላ ክህሎት ባለቤት እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ የቴራዞና የጡብ ምርት ቅንብር(ratio ) የሚሰሩት አሰልጣኝ መምህራን መሆናቸውና የምርት የጥራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ማግኘታቸው የምርታቸው ጥራት በገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዳደረጋቸው የኮሌጁ ዲን ይናገራሉ፡፡ 736 ነባር ሰልጣኝ ያለው የአሶሳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በያዝነው የትምህርት ዘመን የቅበላ አቅሙን በማሳደግ 736 አዳዲስ ሰልጣኞችን ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡ ስልጠናው ፍላጎት መር እንዲሆን ለማስቻል አዳዲስ ሰልጣኞች የባዮሜትሪክስ ምዘና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ የኮሌጁን አሠራር ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ ዲጂታላይዝ ለማድረግ መሠረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን ‹‹የሥልጠና ጥራት የተረጋገጠበት፣ አካባቢውን ችግር የሚፈቱ ቴክኖሎጂዎች በስፋት የሚፈልቁበትና ሥራ ላይ የሚውሉበት ተወዳዳሪና ምርታማ ተቋም የመሆን›› ግባቸውን ለማሳካት መላ የኮሌጁ ማህበረሰብ ቀን ከሌት በትጋት እየሰሩ እንደሚገኙም የኮሌጁ ዲን አቶ ተመስገን ኃይሉ ይናገራሉ፡፡
en_USEN
Scroll to Top