Mols.gov.et

“ትብብሩ ከክህሎት ልማቱ ባለፈ የሁለቱን ሀገራት የረዥም ጊዜ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድግ ነው፡፡” ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር

November 18, 2023
የቻይናው የትምህርት ቴክኖሎጂ ኩባንያ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በትብብር መስራት እንደሚፈልግ አስታወቀ፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የድርጅቱን መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ በዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ላይ እያከናወናቸው ስላለው ተግባራት እና ሀገራዊ የልማት አቅጣጫዎችን አስረድተዋል፡፡ የቤጂንግ ዌዋ የመስመር ላይ (Online) የትምህርት ቴክኖሎጂ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ጃሰን ጂን በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፣ ድርጅታቸው ለትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሥራውን የሚያቀሉ ዲጂታል የትምህርት ቴክኖሎጂዎችን እንደሚያቀርብና በክህሎት ልማቱ ዘርፍ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በትብብር መስራት እንደሚፈልግ ገልፀዋል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ዘርፉ ከፍተኛ ኢንቨስትመን የሚጠይቅ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ጃሰን ጂን በቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና መሰል የሥልጠና ዘርፎች ዘመኑን የዋጁ ‹‹ሲሙሌተሮችን›› በመጠቀም ደረጃውንና ጥራቱን የጠበቀ ሥልጠና መስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡ ክብርት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፣ ድርጅቱ በትብብር ለመስራት ያለውን ፍላጎት አድንቀው ይህም ከክህሎት ልማቱ ባለፈ የሁለቱን ሀገራት የረዥም ጊዜ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድግ ነው ብለዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top