Mols.gov.et

NEWS

ተመራቂ ተማሪዎች ለሥራ ብቁ እንዲሆኑ ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ሊሠራበት እንደሚገባ ተገለፀ

Nov 18 , 2021 

ተመራቂ ተማሪዎች ለሥራ ብቁ እንዲሆኑ ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ሊሠራበት እንደሚገባ ተገለፀ
የኢትዮጵያ ትሠራለች ፕሮግራም የሁለተኛ ዙር የአሰልጣኞች ምረቃ ሥነ ስርዓት ተከናውኗል፡፡ በሥነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎቹ ንግግር ያደርጉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ነቢሃ መሀመድ በአገራችን የሚገኙ 50 ያህል ዩኒቨርሲቲዎች መኖራቸውን ጠቁመው ለሥራ ዝግጁ የሆነ የሰው ኃይል እንዲያፈሩ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን እና ከአሜሪካን ኮሌጅ ኦፍ ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ያሰልጣኞች ስልጠና በኢትዮጵያ ትሰራለች የሥራ ዝግጁነት እና ክህሎት የአምስት ዓመት ፕሮግራም አንዱ መሆኑን የተናገሩት የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ነብዩ ሰሎሞን ዓላማውም በዓለማቀፍ ደረጃ ለሥራ ብቁ የሆኑ ወጣቶችን ማፍራት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
የአሰልጣኞች ስልጠናው አዲስ አበባ እና ድሬዳዋን ጨምሮ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች የተገኙበት እንደሆነ የገለፁት ወ/ሮ አለምፀሐይ ደርሶልኝ የአዳዲስ ሥራ ፈጠራ እና ፕሮጀክቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለሁለተኛ ጊዜ የተመረቁት ሠልጣኞች የጀመሩት ሌሎችን የማብቃት እንቅስቃሴ ለሥራ አጥነት ችግር መፍትሔ እንደሆን ጠቁመዋል፡፡
ስልጠናው ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው በሚወጡ ወጣቶች ላይ ከመደበኛው ትምህርት ውጪ ለሥራ ዝግጁ የሚያደርጉ ክህሎቶች ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ጥናት ተደርጎ የሥልጠና መመሪያዎች ተዘጋጅተው የተጀመረ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የአሜሪካን ኮሌጅ ኦፍ ቴክኖሎጂ ፐሬዝዳንት ዶ/ር አስማማው አጥናፉ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ ወጥነት ያለው ስልጠና የሚሰጡ የሥራ አምባሳደር መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሦስት ዓመታት ውስጥ 400 ሰልጣኞችን ለማፍራት ያለመው ፕሮግራም በመጀመሪያ ዙር 42 በተለያየ የትምህርት ደረጃ ላይ ያሉ ሰልጣኞችን ያሰለጠነ ሲሆን በሁለተኛው ዙር ደግሞ 63 ሰልጣኞች ለሥራ በቁ መሆን ላይ ያተኮር ስልጠና የሚሰጡ ይሆናል፡፡
en_USEN
Scroll to Top