“ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም…
January 20, 2024
“ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም የወጣቶችን የሥራ ብቃትና ተነሳሽነት ለማጎልበት የሚያስችሉ በርካታ ተሞክሮዎች ተገኝተውበታል፡፡”
ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ
‹‹ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም›› ሁለተኛ ዙር ትግበራ በወላይታ ሶዶ ከተማ በይፋ ተጀመሯል፡፡
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ፣ የሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራሙ ወጣቶች በሥራ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን አቅም ከመገንባት አንፃር በርካታ ተሞክሮዎች ተገኝተውበታል ብለዋል፡፡
ፕሮግራሙ በአንደኛ ዙር ትግበራ በአስር ከተሞች ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ ሲሆን ከነዚሁ ከተማ አንዱ በሆነው የወላይታ ሶዶ ከተማ የተሻለ አፈፃፀም መመዝገቡን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው መንግስትና የግሉ ዘርፍ ተቀራርበው ከሠሩ ለወጣቶች ምቹና አስተማማኝ የሥራ ዕድል ማመቻቸት እንደሚቻል በተጨባጭ መስተዋሉንም አስረድተዋል፡፡
ወጣቶቹ የሥራ ላይ ልምምድ እንዲያደርጉ ዕድል ያመቻቹ የግል ተቋማት ባለቤቶች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ከመወጣት አንፃር ላበረከቱት ሚና ያላቸውን ምስጋና ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በመድረኩ ገልፀዋል፡፡
ሁለተኛውን ዙር የፕሮግራሙን አፈፃፀም በተሻለ ሁኔታ ማሳካት እንዲቻልም የሚመለከታችው መንግስታዊ አካላት ሁሉ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡም አሳስበዋል፡፡
በወላይታ ሶዶ ከተማ ሲተገበር በቆየው አንደኛው ዙር ‹‹ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም›› ተሳታፊ ከነበሩ 396 ወጣቶች መካከል 384 ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩ በመድረኩ ተገልጿል፡፡