ብሩህ ሀገር አገፍ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር መካሄድ ጀመረ
November 27, 2025
ብሩህ ሀገር አገፍ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር መካሄድ ጀመረ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት እና ከኤስ ኤን ቪ ሊዌ ፕሮግራም ጋር በትብብር ያዘጋጀው 6ኛው ሀገር አቀፍ ብሩህ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር በዛሬው እለት ተጀምሯል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰለሞን ሶካ የቡት ካምፕ ስልጠናና ውድድር መድረኩ ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት ብሩህ ኢትዮጵያ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር ከአካባቢያቸው አልፈው ሀገርን የመቀየር አቅም ያላቸው፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ትላልቅ ሃሳቦች የሚለዩበት እና አሸናፊ የሆኑ ሀሳቦች በተደራጀ መንገድ ወደ ካምፓኒ እንዲሸጋገሩ አቅማቸው የሚገነባበት ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት 5 ዓመታት በተካሄዱ የፈጠራ ሃሳብ ውድድሮች ከ12 ሺህ በላይ አዳዲስ ሃሳቦች በፌዴራል ደረጃ ቀርበው ችግር ፈቺና መፍትሄ አምጪ ሆነው የተገኙ 1ሺህ 350 የሚሆኑ የፈጠራ ሃሰቦች ለሽልማት መብቃታቸውን ገልጸዋል፡፡
በማወዳደር እና በመሸለም የማይቆመው ብሩህ-ኢትዮጵያ፤ በውድድሩ ከተሸለሙት መካከል 580 የሚሆኑ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች ኢንተርፕራይዝ አቋቁመው በአሁን ወቅት ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እንደቻሉም አስታውቀዋል፡፡
በዘንድርሮ ብሩህ- ኢትዮጵያ 2018 ከመላው የኢትዮጵያ ክፍል የተውጣጡ 251 የሚሆኑ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች እንደሚሳተፉ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው በዘርፉ ባለሙያዎች ተገምግመው የሚያሸንፉ የፈጠራ ሃሳቦች ወደ ካምፓኒ እንዲሸጋገሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ለቀጣይ 10 ቀናት በሚቆየው በዚህ የቡት ካምፕ ስልጠናና ውድድር የሚሳተፉ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች ሃሰባቸውን ይበልጥ ማበልጸግ የሚያስችላቸው ስልጠና፣ የልምድ ልውውጥ እና የኢንዱስትሪ ጉብኝቶችም የተካተቱበት መሆኑን ተመላክቷል፡፡








