Mols.gov.et

በግል ሥራ ስኬታማ የሆኑ ሥራ ፈጣሪ ኢንተርፕረነሮች ልምድና…

December 8, 2023
በግል ሥራ ስኬታማ የሆኑ ሥራ ፈጣሪ ኢንተርፕረነሮች ልምድና ተሞክሮአቸውን ያካፈሉበት መድረክ ተካሄ፡፡ ዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት ለኢንተርፕረነሮች ክፍት ይሁኑ በሮች በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡ የሳምንቱ ፕሮግራም አካል የሆነው በኢትዮጵያ በግል ሥራ ስኬታማ የሆኑ ሥራ ፈጣሪ ኢንተርፕሪነሮች እና ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች የተሳተፉበት የልምድ ልውውጥ እና የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን፤ ኢንተርፕሪነሮች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት እና ሥነ ምህዳሩ ለኢንተርፕረነርሺፕ የተመቸ ለማድረግ ከህዳር እስከ ህዳር የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ቢቆይም ሳምንቱ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረወን የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት አስመልክቶ በልዩ ሁኔታ ከሥራ ፈጣሪዎች ምክክር የሚደረግበት፣ ልምድና ተሞክሮ ልውውጥ የሚከናወንበት፣ ኢንተርፕረነሮች በሚጋጥሟቸው በተግዳሮቶች እና መውጫ መንገዶች ዙሪያ ምክክር የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሳምንቱ ባለፈው ዓመት ሚሊዮን ፈተናዎች ሚሊዮን ዕድሎች በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መርሃ ግብሮች መከበሩን ያስታወሱት ሚንስትር ዴኤታው ዘንድሮ ለኢንተርፕረነሮች የማይመቹ የተዘጉ በሮች በመኖራቸው እነዚህ የተዘጉ በሮች እንዲከፈቱ እና እንቅፋቶች እንዲቀረፉ ታሳቢ በማድረግ ለኢንተርፕረነሮች ክፍት ይሁኑ በሮች በሚል መሪ መልዕክት ባለድርሻ አካላትን በሳተፉ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሃሳን ሁሴን በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ዘርፉ ትኩረት የተነፈገው እንደነበር አስታውሰው በአሁን ወቅት በተለይ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መመራት ከጀመረ በኋላ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት እየተደገፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በመድረኩ በግል ሥራ ፈጠራ ተሰማርተው ሥኬታማ የሆኑ ኢንተርፕረነሮች ልምድና ተሞክሮአቸውን ያጋሩ ሲሆን በተለይ በጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ደረጃ የሚያጋጥሙ ችግሮች እና መፍቴሄዎቻቸው ላይ ያተኮረ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
en_USEN
Scroll to Top