በዓለም ላይ ያለውን ሰፊ የሥራ ገበያ ለመጠቀም ህጋዊ አሠራሮችን መከተል፣ ተቋማዊ አቅምን ማጎልበትና አደረጃጀትን ማሻሻል ያስፈልጋል ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
August 16, 2025
በዓለም ላይ ያለውን ሰፊ የሥራ ገበያ ለመጠቀም ህጋዊ አሠራሮችን መከተል፣ ተቋማዊ አቅምን ማጎልበትና አደረጃጀትን ማሻሻል ያስፈልጋል
ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ከሚያከናውናቸው አበይት ተግባራት መካከል ዜጎች በውጭ ሀገራት ከሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል አንዱ ነው፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ በራሱ አቅም ባለማው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት አማካኝነት የዜጎችን መብት፣ ደህንነት፣ ተጠቃሚነትና የሥራ ዋስትና ማዕከል ባደረገ መልኩ የሥራ ስምሪቱ እንዲፈፀም እያደረገም ይገኛል፡፡
አስቀድመው ይስተዋሉ የነበሩ የአሠራር ማነቆዎችን ለማስወገድ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች በሚኒስቴር መ/ቤቱ እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡ ዘርፉ ይመራበት የነበረውን የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ የማሻሻል ሥራም ተሠርቷል፡፡
ዜጎችን ወደ ውጭ ሀገራት ለሥራ ከሚልኩ የአሠሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር ተቀራርቦ መሥራት ሌላው በሚኒስቴር መ/ቤቱ ትኩረት የተሰጠው ተግባር ሲሆን በዚሁ መሰረት ቁጥራቸው ከ 6መቶ ከሚልቁ የኤጀንሲ አመራርና ባለቤቶች ጋር በ2018 ዕቅድና በተሻሻለው የውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት አዋጅ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ኤጀንሲዎችን አቅም በማዳበርና ተቋማዊ ቁመናቸውን በማሻሻል ለዘርፉ ምቹ ስነ ምህዳር ለመፍጠር ሚኒስቴር መ/ቤቱ በትኩረት እሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
በውጭ ሀገራት በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ለመሠማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ምክክርና ውይይት ለማካሄድ መድረኩ መዘጋጀቱንም ክብርት ሚኒስትር ጠቁመዋል፡፡
ወደ ውጭ ሀገር የሚካሄዱ ሥራ ስምሪቶች የኢትዮጵን ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም የዜጎችን መብትና ደህንነት ባከበረ መልኩ መካሄድ ይኖርባቸዋል ያሉት ክብርት ሚኒስትር ከህገወጥ ድርጊቶች መራቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በዓለም ላይ ያለውን ሰፊ ገበያ ለመጠቀም ህጋዊ አሠራሮችን መከተል፣ ተቋማዊ አቅምን ማጎልበትና አደረጃጀትን ማሻሻል እንደሚገባም በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡










