በክህሎት ልማት ዘርፍ ግንባር ቀደም ለሆኑ ኢንዱስትሪዎች እውቅና ተሰጠ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ንግድ ማህበራት ምክር ቤት እና ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት በትብብር የተዘጋጀው የመጀመሪያው በክህሎት ልማት ላይ ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወቱ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች እውቅና ሰጥቷል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት፤ የእውቅና ኘሮግራሙ የተዘጋጀው በክህሎት ልማት ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር እና በዘርፉ አበረታች ስራ የሰሩ ኢንዱስትሪዎች ለበለጠ ስራ እንዲነሳሱ ላበረከቱት አስተዋጽዎ እውቅና ለመስጠት ነው።
መድረኩ የኢንዱስትሪዎች ፍላጎት እና የመንግስት አቅርቦት ላይ ያሉ ጉድለቶችን በጋራ በመለየት ተቀራርቦ ለመስራት የሚያግዝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ማህበራት ምክርቤት ኘሬዝዳንት ኢንጅነር መላኩ አዘዘ በበኩላችው፤ በክህሎት ልማት ላይ የግሉ ዘርፍ ጠንካራ ተሳትፎ በዘርፉ ፈጠራን በማበረታታት ዘላቂ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ ያግዛል ብለዋል።
በመድረኩ የግሉ ዘርፍ እና መንግስት የተሳተፋበት የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን በክህሎት ልማት ዘርፍ የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ 24 ኢንዱስትሪዎች የእውቅና ሰርተፍኬት እና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።